//የፓስተር ዳዊት ስህተቶች// "እምነት - TopicsExpress



          

//የፓስተር ዳዊት ስህተቶች// "እምነት እና ሥራ የአንድ ርግብ ሁለት ክንፍ ናቸው" ዘና ብላችሁ ተቀመጡና እስኪ ባለሁበት ሀገር የታዘብኩትን አንድ ታሪክ ላውጋችሁ። ነጋዴ መነኩሴ አይደለም ለጽድቅ አይሰራም በል ትላንት መፅሐፍ የገዛህበትን ገንዘብ ክፈለኝ ብሎ አንዱ ወዳጄ ገና በጠዋቱ ፈገግ አስባለኝ። ወዳጄ እንዳለው መነኩሴ ለጽድቅ ይሰራል። ባለሁባት ሀገር ደግሞ ፈረንጆቹ ቤተክርስቲያን እየሄዱ የሚያገለግሉት ለሥራ ብቻ ነው። አንድ ሰው ቢሮው ገብቶ ስራ እንደሚሰራ ለእነሱ ቤተክርስቲያን ቢሯቸው ናት። የሚሰሩትን ነገር ሁሉ አያምኑበትም። ታድያ የማታምኑበትን ነገር ለምን ትሰራላችሁ ? ስንላቸው this is my profession ይህ የኔ ስራ ነው ይላሉ። ይህ በእጅጉ ያስገርማል። ሥራ እንጂ እምነት የላቸውም። አንዳንዶቹ ደግሞ እምነት ሳይኖራቸው በጎ ነገር መስራት ያስደስታቸዋል። ፈረንጆቹ ታዳጊ ሀገራትን የሚረዱት ለመጽደቅ አይደለም። ስደተኛን የሚረዱት ልዩ ልዩ በጎ ነገርን የሚሰሩት ለመጽደቅ ሳይሆን ለሰብአዊነት ለሕሊናቸው እርካታ ነው። ሐዋርያው እምነትና በጎ ሕሊና ይኑርህ እንዳለ ብዙዎቹ እምነት ባይኖራቸው በጎ ሕሊና አላቸው። ብዙዎቹ ጓደኞቼ እግዚአብሔር አለ ብለው አያምኑም። አንዳች እምነት የላቸውም በጎ ሥራ ግን አላቸው። ነገር ነገርን ያነሳል እንዲሉ እዚህ ጋ ፩ድ ነገር ላንሳ ! አንዳንዶች ሥርዓትን በተመለከተ ፓስተር ዳዊት ለምን እንዲህ እየዘለለ ያስተምራል እያሉ ቪዲዮ ይልኩልን ነበር። አሁን ስለሱ አላወራም። ለዛሬ ሥርዓቱን ትተን እስኪ ትምህርቱን እንፈትሽ። ፓስተሩ ኢየሱስ የሚለውን ቃል ብትጠራ በቃ ትድናለህ በኢየሱስ ብቻ ማመን ይበቃናል። የምን ነገር ማብዛት ነው ሲል ሰማሁትና ተገረምኩ። ፓስተሩ ቀጠለና 38 ዓመት ሙሉ መጻጉ ለመፈወስ ሲጠብቅ ክርስቶስ በ 38 ሰከንድ አዳነው። እናንተም ለመዳን 38 ዓመት አትጠብቁ ብሎ መከረን። እግዚአብሔር አዳምን ለማዳን ፭ ሺሕ ፭ መቶ ዘመን እንዴት ፈጀበት ብዬ ፓስተሩን ለመጠየቅ አሰብኩና ተውኩት። አንድ ጥቅስ ይዞ መብረር የብዙዎች ችግር ነውና በዚሁ እንለፈው። በነገራችን ላይ ፓስተሩን ለማቃለል በጥላቻ ለማየት ዓላማችን አይደለችም። ትምህርቱን ስንፈትሽ ግን ብዙ ስህተቶችን አገኘን። በአፋችሁ ኢየሱስ ብትሉ በቃ ዳናችሁ ብሏልና ይህን ቃል እንዴት ሳያነበው ለመስበክ ተነሳ? በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ ፊልጵስዩስ 2 ፦12 ለመዳን ገና እስከ መጨረሻው ድረስ ደም እስከማፍሰስ ድረስ መታገል አለብን። ዕብራውያን 12 : 4 ከኃጢአት ጋር እየተጋደላችሁ ገና ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም እንዲል። የመዳን ቀን ዛሬ ነው ብዙዎች ድነናል ተፈጽሟል የመዳን ቀን ዛሬ ነው እያሉ እግራቸውን ሰቅለው ለመቀመጥ ይወዳሉ። ጳውሎስና ጴጥሮስ እስጢፋኖስና ያዕቆብ ያን ሁሉ መከራ መቀበል ለምን አስፈለጋቸው? የትኛው ሐዋርያ ነው ዳንኩ ተፈጸመ ብሎ ተዝናንቶ የኖረው? ፓስተር ዳዊት እንደመከረን በሰከንድ ከዳንን ሁሉም ዘሎ መንግሥተ ሰማይ በገባ ነበረ! ለመዳንማ ገና እስከ መጨረሻው መፅናት ያስፈልጋል። እስከ መጨረሻው የጸና ይድናል እንዲል። በቃ ድነናል ተፈጸመ እያሉ በምድራዊ ገነት የሚኖሩ ሰዎች አሉ። እንኳን በምድር በሰማይ ያለውም ሰይጣን መውደቁን እንዴት አልሰማችሁም? የቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ የተባለውን እንዴት አልሰማችሁም? ከዘላለም ሞት ድነናል። የዘላለም ሞት ያ ድሮ ቀረ። አሁን ግን በስጋችን ፈቃድ ልዩ ልዩ ኃጢአትን ብናፈቅር እንደ ይሁዳ ክርስቶስን ብንክድ ያለ ጥርጥር መጨረሻችን ሞት ናት። ለዚህ ነው ሐዋርያው መዳናችሁን በትጋት ፈጽሙ ያለው። ኦርቶዶክስ ክርስቲያን እምነትንና ሥራን አስተባብራ ታምናለች። ዓይነ ስውሩ ታምናለህን ተባለና ካመነ በኋላ ሔደህ በሰሊሆም መጠመቂያ ተጠመቅ የተባለው እምነት እና ሥራ የአንድ ርግብ ሁለት ክንፍ ስለሆኑ ነው። መቼም አይለያዩምና! ፕሮቴስታንት ዘመዶቻችን ሆይ እምነት ያለ ሥራ ያድናልን?
Posted on: Mon, 08 Jul 2013 11:41:26 +0000

Trending Topics




© 2015