By ድምፃችን ይሰማ #Ethiopia - TopicsExpress



          

By ድምፃችን ይሰማ #Ethiopia #EthioMuslims ትግላችን ኢትዮጵያዊ ነው! እሁድ ነሐሴ 5/2005 ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ከመላው አለም ሙስሊሞች ጋር በእምነት ብንመሳሰልም በጉልህ የሚታወቁ ልዩ ባህርያቶች አሉን፡፡ እንደ አገር እስልምናን ከመካ በመቀጠል በሁለተኛነት ተቀብለን ማመናችን የልዩ ባህሪያችን መነሻ ነው፡፡ መንግስት መራሹን አህባሻዊ የግዳጅ አስተምህሮ ከህገወጥነቱ ባለፈ አምርረን የምንቃወመውም ኢትጵያውያንን ለእስልምና ባዳ አድርጎ የመቁጠር አባዜ የተጠናወተው በመሆኑ ጭምር ነው፡፡ በዛሬዋ ኢትዮጵያችንም ቢሆን ይህ ልዩ ባህሪያችን ይበልጥ እያደገ እንጂ እያነሰ ሲመጣ አይታይም፡፡ አመት ከመንፈቅ የሞላው የእምነት መብት ማስከበር ትግላችን ነባሩን ልዩ ኢትዮጵያዊ ባህሪያችንን ይበልጥ ለአለም ያስተዋወቀ ሆኗል፡፡ የችግራችን ምንጭ የሆነው በኢትዮጵያችን የእምነት ነፃነት ማጣታችን ነውና ያነሳናቸው ሶስት ጥያቄዎች በዜግነታችን እና በህገ መንግስቱ መሰረት ልናገኛቸው የሚገቡን ንፁህ መብቶቻችንን ነው፡፡ የመረጥነው ህጋዊ አካሄድም የኢትዮጵያን ህገ መንግስት እና ባህላዊ እሴት መሰረት ያደረገ ነው፡፡ የምንጠቀማቸው የተቃውሞ መንገዶች ፍፁም ኢትዮጵያዊ ናቸው፤ የምንፈልገው መፍትሄም እንዲሁ! ይህ ደግሞ ትግላችንን ሌላ ስም ለማሰጠት ብዙ የደከሙ አካላትን አንገት ያስደፋና እኛም የምንኮራበት መገለጫችን ነው፤ ይህ እንደሆነም ይዘልቃል! ኮሚቴዎቻችን ለወራት ከመንግስት ጋር ሲደራደሩ ውክልናቸው የተጠረጠረበትም ሆነ ከጀርባቸው የያዙት ሌላ አጀንዳ አለ ተብሎ ክስ የቀረበበት አንድም ወቅት አልነበረም፡፡ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ከኮሚቴዎቻችን ጋር ውይይት ባደረገባቸው ግዜያት ህጋዊነታቸውን አፅድቆ ህገወጡ መጅሊስ ‹‹አክራሪ›› እና ‹‹ድብቅ አላማ ያላቸው›› ማለቱ አግባብ ባለመሆኑ ከአሁኑ በኋላ እንደሚያስቆም ቃል ገብቶም ነበር፡፡ ከዚህም አልፎ ከኮልፌ ቀራንዮ ኮማንድ ፖስት ለኮሚቴው በቀረበው ጥያቄ መሰረት የክፍለ ከተማው ፖሊስ አዛዥ፣ የክፍለ ከተማው ፍትህ ቢሮ ኃላፊ፣ የክፍለ ከተማው የፌዴራል ፖሊስ ተወካይና የክፍለ ከተማው የብሄራዊ ደህንነትና መረጃ ቢሮ ኃላፊ ባደረጉት ስብሰባ የስራ ሃላፊዎቹ በአወሊያ እየተካሄደ ያለውን ተቃውሞ ሲገልፁ እንዲህ ብለው ነበር ‹‹ሂደቱ እጅግ ሰላማዊ ነው፤ በሃገራችን የሚካሄድ የሰለጠነ ሰላማዊ ሂደት ነው፤ ሁላችንም አርብ አርብ በአወሊያ እንገኛለን፤ እንዳየነው ችግር ይፈጠራል ብለን በጭራሽ አንሰጋም፤ እኛን የሚያሳስበን መች ያቆማል (ያበቃል)? የሚለው እና ከእናንተ እጅ ወጥቶ የሌሎች መጠቀሚያ እንዳይሆን ከመስጋታችን በስተቀር‹‹ ነበር ያሉት፡፡ በዚህ የደህንነት ሀላፊዎች ራሳቸው በይፋ በመሰከሩለት ኢትዮጵያዊ ትግል ላይ ነው እንግዲህ ከየካቲት 26 በኋላ ‹‹አረቦች በአንዋር ሲቀሰቅሱ መያዛቸው የእንቅስቃሴውን ድብቅ አላማ ያሳያል›› የሚል የሀሰት ውንጀላ የተሰነዘረበት፡፡ ትናንት ያሞገሱትን ትግል ነው ‹‹የኮሚቴው አባላት ውጭ ሃገር ሄደው መምጣታቸው ድብቅ አላማ እንዳለው ያሳያል›› ሲሉ ለማጠልሸት የሞከሩት፡፡ ያንኑ ሰላማዊ ትግል ነው ኢትዮጵያዊው ሙስሊም ከወሬ ባለፈ ከማያውቃቸው ማሊ እና ናይጄሪያ ካሉ ቡድኖች ጋር ለማስተሳሰር ሲሞከሩ ያደመጥነው፡፡ በቅርቡም ከባንዲራ ጋር ተያይዞ ሙስሊሞች ጸረ ኢትዮጵያ አቋም ነው ያላቸው የሚል ያልበሰለ ሙግት ይዞ የግዳጅ ሰልፍ ሲያስወጣበት ነበር፤ በሚዲያ ሲያስለፍፍበት ነበር፡፡ የጨነቀው እርጉዝ ያገባል እንዲሉ ትግሉን መንግስት ከሚፈልጋቸው አገራት ጋርም ሲያያዝ ከርሟል፡፡ ካሁን ቀደም ደጋግመን እንደገለጽነው ሁሉ ለኢትዮጵያዊ ችግራችን ኢትዮጵያዊ መፍትሄ እንፈልጋለን! ኢትዮጵያዊ ወኔያችን የዜግነት መብታችንን ለማስከበር እንደሚያንስ መጠራጠር በኢትዮጵያዊ ማንነት ላይ መቀለድ ነው! ለአመፅ እየገፋችሁን ጥርሳችንን ነክሰን ጠብቀን ያስቀጠልነውን ሰላማዊ ትግላችንን በሃገራዊነቱ ልትኮሩበት ሲገባ ለሃገር አደጋ አድርጋችሁ መሳላችሁ ለኢትዮጵያችን በተሰዉ እና እየደከሙ ባሉ ዜጎች ላይ ማፌዝ ነው! ላነሳናቸው ቀላል የዜግነትና የመብት ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት አለመቻል ኢትዮጵያን በኢትዮጵያዊ ባህሪዋ ጠብቆ ለማቆየት ፍቃደኝነት አለመኖር ካልሆነ ሌላን ሊያመላክት አይችልም! አዎን! የኮሚቴዎቻችንን ንግግር ደግመን እንናገራለን! ‹‹የሃሰት ፕሮፖጋንዳ መደጋገም የመብት ጥያቄን ወንጀል አያስብለውም!›› ጥያቄዎቻችን እስኪመለሱ ሰላማዊ ትግላችን በታላቅ አገራዊ ወኔ ይቀጥላል፤ ድልም ከአላህ እንጂ ከሌላ አይደለምና! አላሁ አክበር!
Posted on: Sun, 11 Aug 2013 11:24:16 +0000

Trending Topics



Recently Viewed Topics




© 2015