Ethiopia to send its public diplomacy delegates to Egypt - - TopicsExpress



          

Ethiopia to send its public diplomacy delegates to Egypt - ኢትዮጵያ የሕዝብ ዲፕሎማሲ የልዑካን ቡድን ወደ ግብጽ ልትልክ ነው የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ የሕዝብ ዲፕሎማሲ የልዑካን ቡድን ወደ ግብጽ እንደሚልክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴድሮስ አድሓኖም አስታወቁ። የግብጽ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ ከሁለት ሳምንት በኋላ ኢትዮጵያ በመምጣት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሚኒስትሩ ዶክተር ቴርድሮስ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት የልዑካን ቡድኑ ወደ ግብጽ የሚያደርገው ጉዞ ከአገሪቱ ጋር ያለውን ግኑኝነት ወደ አዲስ ምዕራፍ በማሸጋገር የህዝብ ለህዝብና አጠቃላይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን ለማጠናከር ነው። መንግሥት የልዑካን ቡድኑን የሚልከው ኢትዮጵያ ከግብጽ ጋር መተማመን በመፍጠር ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ካላት ፍላጎት የተነሳ መሆኑን ዶክተር ቴድሮስ አስረድተዋል። በቅርቡ ወደ ግብጽ የሚያቀናው የህዝብ የልዑካን ቡድን ከህዝብ ክንፍ፣ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከኃይማኖት ተቋማት፣ ከታዋቂ ሰዎች፣ ከግሉ ዘርፍ፣ ከመንግሥትና ከግል መገናኛ ብዙኃን፣ ከኪነ-ጥበብና ከሌሎችም የተውጣጡ አባላት እንደሚሆኑ ገልጸዋል። የልኡካን ቡድኑ ከግብጽ አቻው ጋር በመሆን የሁሉቱን አገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶችን የሚያጠናክር ውይይት እንደሚያደርግም ሚኒስትሩ ተናግረዋል። በሌላ በኩል አዲሱ የግብጽ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ ከሁለት ሳምንት በኋላ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር አዲስ አበባ ላይ ተገናኝተው እንደሚመክሩ ዶክተር ቴድሮስ ጠቁመዋል። ሁለቱ መሪዎች ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ጨምሮ የአገራቱት ግንኙነት በሚጠናከርባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እንደሚመክሩ ነው ሚኒስትሩ ያመለከቱት። አዲሱ የግብጽ ፕሬዝዳንት አል ሲሲ የግድቡ ጉዳይ በውይይት ብቻ እንዲፈታ የያዙት ሃሳብ የኢትዮጵያ መንግሥት ፍላጎትና ለረጅም ጊዜ ይዞት የቆየ አቋም በመሆኑ ተቀባይነት እንዳለው አመልክተዋል። ኢትዮጵያ በግድቡ ዙሪያ ያለው አለመግባባት በውይይት ብቻ እንዲፈታ የያዘቸው አቋም በዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ ተቀባይነት እንዳለው በመግለጽ በግብጽ በኩል ይኸው ፍላጎት መንጸባረቁም እንደበጎ ጅምር የሚወሰድ ነው ብለዋል። ፕሬዝዳንት አል ሲሲ የግድቡ መገንባት በኢትዮጵያና በግብጽ ግንኙነት ላይ ችግር እንደማይፈጥር መግለፃቸው ትልቅ ለውጥ እንደሆነ ነው ዶክተር ቴድሮስ የተናገሩት። ኢትዮጵያ ግብጽ ከዓባይ የምታገኘውን የውኃ መጠን መቀነስ እንደማትፈልግና ግድቡ ለኃይል ማመንጫነት ብቻ እንደምታውለው በመግለጽ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የግብጽ የመገናኛ ብዙኃን በግድቡ ዙሪያ በሚያቀርቡት ዘገባ አዎንታዊ ሽፋን መስጠት መጀመራቸውም ዶክተር ቴድሮስ ሳይጠቁሙ አላለፉም። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴድሮስ አድሓኖም ባለፈው ሳምንት ካይሮ ውስጥ በተካሄደው የፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አል ሲሲ በዓለ ሲመት ላይ ከተገኙ በኋላ ከፕሬዝዳንቱ ጋር በታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ዙሪያ መወያየታቸው ይታወሳል። ኢዜአ
Posted on: Thu, 12 Jun 2014 09:30:00 +0000

Recently Viewed Topics




© 2015