“አኮ መኖዬ”ን በጨረፍታ (አፈንዲ - TopicsExpress



          

“አኮ መኖዬ”ን በጨረፍታ (አፈንዲ ሙተቂ) ------ በኦሮሞ ህዝብ አፈ-ታሪክ በስፋት ከሚታወቁ ገጸ-ባህሪዎች መካከል ናት -አኮ መኖዬ፡፡ወደ የትኛውም የኦሮሚያ ዞን ብትሄዱ እርሷን የማያውቃት ሰው አታገኙም፡፡ በዚያ ላይ የእያንዳንዱ ዞን ነዋሪ “አኮ መኖዬ የኛ አካባቢ ሰው ናት” ይላችኋል፡፡ ቦረና ብትሄዱ “አኮ መኖዬ የዚህ አካባቢ ገዥ ነበረች፤ የኖረችበትን ሰፈርና የሞተችበትን ስፍራ ላሳይህ እችላለሁ” የሚል ሰው ይገጥማችኋል፡፡ ሸዋ ብትሄዱም “አኮ መኖዬ እዚሁ ነበረች እኮ” ትባላላችሁ፡፡ ወደ ሀረርጌ ብትመጡ ደግሞ “አኮ መኖዬ በጨርጨር አውራጃ ለገ-ቤራ በሚባለው አካባቢ ነው የኖረችው” የሚል የረዥም ጊዜ አፈ-ታሪክ አለ፡፡ ከዚህ እንደምንረዳው አኮ መኖዬ የኦሮሞ ህዝብ እንደ አሁኑ ተስፋፍቶ በሀይማኖትና በዘዬ ከመለያየቱ በፊት የነበረች ጥንታዊ ሴት ናት፡፡ የቅርብ ዘመን ሰው ብትሆን ኖሮ ታሪኳ በሁሉም የኦሮሚያ ዞን ሊታወቅ ባልቻለ ነበር፡፡ --- ያቺ በትውፊት በስፋት የምትታወቀው አኮ መኖዬ ጨካኝ ንግሥት ነበረች፡፡ በጭካኔ እርምጃዋ ብዙ ሰዎችን ፈጅታለች፡፡ ታዲያ ሰዎችን የምትገድለው እንዲሁ ከመሬት ተነስታ አይደለም፡፡ በቅድሚያ የሀገሬው ነዋሪዎች በጭራሽ ሊተግብሯቸው የማይችሏቸው ነገሮች እንዲደረጉላት ትጠይቃለች፡፡ ፍላጎቷ እርሷ በጠየቀችው መንገድ ካልተፈጸመላት በአንድ ቀን መቶ ሰዎችን ትጨርስና ታስቀብራለች (አፈ-ታሪኩ ከቦታ ቦታ ይለያያል፤ “በአንድ ጊዜ መቶ ሰው ትገድላለች”፤ “አንድ ሰው ትገድላለች”፤ “አስር ሰው ትገድላለች” እየተባለ ይነገራል)፡፡ አኮ መኖዬ ከጠየቀቻቸው ጥያቄዎች አንዱ “ከብቶች እንዳይሰማሩ፤ ከቤትም እንዳይውሉ” የሚለው ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ጥያቄ እንዴት ነው የሚመለሰው?… እርሷም የምትፈልገው ይህንኑ ነውና በአንድ ቀን መቶ ሰው ጨፈጨፈች፡፡ በሌላ ቀን ደግሞ “መሬትም ያልነካ ሰማይ ላይም ያልወጣ፤ አየር ላይ የተንሳፈፈ ቤት ስሩልኝ” አለች አሉ፡፡ ጥያቄዋ መላሽ ቢያጣ መቶ ሰው በአንድ ላይ ረሸነች፡፡ እንደገና ደግሞ “የቅቤ ተራራ ስሩልኝ፤ ይህ ተራራ ከተሰራ በኋላ ሳይናድ መቆየት አለበት” በማለት አዘዘች፡፡ በሰፈሩ ውስጥ ያለው ቅቤ ተሰብስቦ መለስተኛ ተራራ በጧት ተሰራ፡፡ ነገር ግን ጸሐይ እየጠነከረች ስትሄድ የቅቤ ተራራው ቀልጦ ፈሰሰ፡፡ አኮ መኖዬም እንደለመደችው መቶውን ሰው ፈጀች፡፡ አኮ መኖዬ እንዲህ እንዲህ እያደረገች ህዝቡን ስትጨርስ ሰነበተች፡፡ በመጨረሻም ሲያቀብጣት “በአየር ላይ የሚበር ፈረስ አምጡልኝ” የሚል ትዕዛዝ አወጣች፡፡ በዚህን ጊዜ የሰው እልቂት ያስመረራቸው የሀገሩ “ሀዩዎች” (አዋቂዎች) ተመካከሩ፡፡ ሴትዮዋን የሚያስወግዱበትን ብልሃት ለመፈለግ መላ መቱ፡፡ የአኮ መኖዬን ገመና የተረዳ አንዱ ውስጠ አዋቂ “ይህች ንግሥት የሜዳ አህያ አይታ አታውቅም፤ ስለዚህ ለምን በርሱ ላይ አስቀምጠናት ከገደል ገብታ እንድትሞት አናደርግም?” በማለት ተናገረ፡፡ ሌሎቹ ተሰብሳቢዎች ሰውዬው ባመጣው ዘዴ ተስማሙ፡፡ የሜዳ አህያ ተፈልጎ እንዲመጣም አዳኞች ወደ “ዲዳ” (የሳር ሜዳ) ተላኩ፡፡ የሜዳ አህያው ተይዞ መጣና ለአኮ መኖዬ ቀረበላት፡፡ ታዲያ አዋቂዎቹ የሜዳ አህያውን ሲያቀርቡላት እንዲህ የሚል ቃል አክለው ነገሯት፡፡ “ይህ ፈረስ በአየር ላይ ለመብረር የሚችለው ፊቱ በጨርቅ ከተሸፈነ ብቻ ነው”፡፡ አኮ መኖዬም ከሰዎቹ የተነገራትን ስትሰማ የእውነት መሰላት፡፡ በሃሳቡ መስማማቷን ገለጸችና የሜዳ አህያው በጨርቅ ተሸፈነ፡፡ እርሷም ተፈናጥራ ከጀርባው ላይ ወጣች፡፡ የሜዳ አህያው ከእስር ሲለቀቅ እንደ ጀት በረረ፡፡ ዳሩ ምን ያደርጋል?.. የአኮ መኖዬን ሰማይ ላይ የመውጣት ህልም ሳያሳካላት ከገደል ውስጥ ገባ፡፡ እርሷም ሆነ አህያው በአንድ ላይ ተሰባብረው ሞቱ፡፡ በዚህም መንገድ በጭቆናዋ የታፈነው ህዝብ ከስቃዩ ተገላገለ፡፡ -- አፈንዲ ሙተቂ መስከረም 4/2007 ----- ማስታወሻዎች 1. የአኮ መኖዬ አፈ-ታሪክ በሲዳማ ህዝብ ትውፊትም በደንብ ይታወቃል፡፡ ሆኖም በሲዳማዎች የምትታወቅበት ስም ከዚህ የተለየ ነው (ስሟን ረስቼዋለሁ፤ እስቲ አስታውሱኝ)፡፡ 2. ስለ አኮ መኖዬ አሟሟት የሚነገረው ታሪክ ከቦታ ቦታ ይለያያል፡፡ በሀረርጌና በቦረና ግን አሟሟቷ ከላይ በተገለጸው መንገድ እንደተፈጸመ ነው የሚነገረው፡፡ 3. አንዳንድ ምሁራን “የአኮ መኖዬ ታሪክ ሴቶች ወደ ስልጣን እንዳይመጡ ለመከላከል የተፈጠረ ሳይሆን አይቀርም” የሚል ግምት አላቸው፡፡ ነገር ግን ግምቱ ትክክል አይመስለኝም፡፡ በኦሮሞም ሆነ በሌሎች ህዝቦች አፈ-ታሪክ በከፍተኛ ተምሳሌትነታቸው የሚወሱ የሴት ነገሥታት አሉ፡፡ በአንጻሩም በጭካኔያቸው የሚኮነኑ የወንድ መሪዎች ብዙ ናቸው፡፡ ስለዚህ ለትውፊቱ ሌላ ግምት ከመስጠት ይልቅ የሞራል ዋጋን ለማስተማር የተፈጠረ ተረት አድርጎ መቀበሉ የተሻለ ይመስለኛል፡፡ -------
Posted on: Sun, 14 Sep 2014 21:29:56 +0000

Trending Topics



ass="stbody" style="min-height:30px;">
And I am not saying this because I feel neglected, for I have
ews Published:
BoxWave Capacitive HP Veer 4G Stylus (Bold Orange) You can find

Recently Viewed Topics




© 2015