አፈንዲ ሙተቂ/Afendi Muteki- Ethnographic Researcher and - TopicsExpress



          

አፈንዲ ሙተቂ/Afendi Muteki- Ethnographic Researcher and Author ረመዳን በታሪክ ውስጥ (አንድ) -------- ረመዳን የጾም ወር ከመሆኑ ባሻገር በርካታ ታሪካዊ ክስተቶች የተስተናገዱበት ነው። ከነርሱም መካከል በቀዳሚነት ተጠቃሽ የሆነው “ከረመዳን በሻገር” በሚለው የትላንቱ ጽሑፍ ውስጥ የተወሳው የነቢዩ ሙሐመድ መልዕክተኛነት የታወጀበት ታላቅ ክውን ነው። በርግጥም ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ወህይ (ራዕይ) ማየት የጀመሩት በወርሃ ረመዷን ነው። ከርሱ ባሻገርስ ረመዳን ምን ዓይነት ክስተቶችን አስተናግዷል? ለዛሬ አንዱን ላውጋችሁ። ***** ***** ***** “የቅዱስ ቁርኣን ሱራዎች በወረዱበት ቅደም ተከተል መሰረት ያልተቀመጡት ለምንድነው?” የሚል ጥያቄ መጥቶባችሁ ያውቃል? እንዲያ ከሆነ ምክንያቱ የሚከተለው ነው። ሼኽ ሰይድ ሙሐመድ ሳዲቅ እና ሐጂ ሙሐመድ ሣኒ ሐቢብ ባዘጋጁት የቅዱስ ቁርኣን የአማርኛ ትርጉም መቅድም ላይ “የቁርአን ወህይ ሁለት ደረጃዎች ነበሩት” ይላሉ። አንደኛው ቁርኣኑ ለጂብሪል የወረደበት ደረጃ ነው። ሁለተኛው በ23 ዓመታት ውስጥ በነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ላይ የወረደበት ደረጃ ነው። ቁርኣን ከፍጥረተ ዓለም መገኘት በፊት በለውሀል ማሕፉዝ (የተጠበቀው ሰሌዳ) ላይ ተጽፎ ነበር። በማስከተልም ጂብሪል ቤይተል ማዕሙር በሚባለው ሰማያዊ የመላኢካዎች (መላእክት) መሰባሰቢያ ቤት ውስጥ ሳለ ሙሉው መጽሐፍ ወርዶለታል። የቁርኣን ሱራዎችና አያዎች (አንቀጾች) የተሰባሰቡት ሙሉው ቁርኣን ለጂብሪል በወረደበት ቅደም ተከተል መሰረት ነው። ከዚያም ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በመልዕክተኝነት ከተላኩ በኋላ ጂብሪል በነቢዩና በተከታዮቻቸው ህይወትና የትግል ጎዳና ላይ የተከሰቱ እጅግ አስፈላጊ ሁኔታዎችና አጋጣሚዎችን እየጠበቀ ሁሉንም የቁርኣን ሱራዎች በ23 ዓመታት ውስጥ በማውረድ አጠናቆአቸዋል። ታዲያ ቁርኣን ከለውሀል ማሕፉዝ ወደ ጂብሪል የወረደው በወርሃ ረመዷን በከፍተኛይቱ ሌሊት (ለይለቱል ቀድር) መሆኑን ልብ በሉ። በዚህች ሌሊት ስም የተሰየመው የቁርኣን ሱራ (አል-ቀድር) የመጀመሪያው አንቀጽ (አያህ) ይህንኑ እውነታ ያረጋግጣል። (ምንጭ፡ “ቅዱስ ቁርአን”፡ የአማርኛ ትርጉም በሰይድ ሙሐመድ ሳዲቅና በሐጂ ሙሐመድ ሣኒ ሐቢብ፣ አዲስ አበባ፣ 1961፡ ገጽ 9)
Posted on: Sat, 13 Jul 2013 02:45:46 +0000

Trending Topics



Recently Viewed Topics




© 2015