የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት (ክፍል - TopicsExpress



          

የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት (ክፍል አምስት) ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ ---- በትናንትናው ጽሑፍ የተወሰኑ ስህተቶችን ፈጽሜአለሁ፡፡ አንደኛው ኢትዮጵያ የአሜሪካ ተቋማትን ከዘጋች በኋላ የሶቪየትን መሳሪያ አገኘች የሚለው ነው፡፡ ነገሩ እርግጥ ነው፡፡ ሆኖም መሳሪያው ወደ ኢትዮጵያ የመጣበት ጊዜ እኔ ከገለጽኩት የተለየ ነው፡፡ ማለትም በሀምሌ 1969 ሶማሊያ ወረራውን ስትጀምር የሶቪየት መሳሪያ ወደ ኢትዮጵያ አልመጣም፡፡ ኢትዮጵያ ከሐምሌ 1969-ህዳር 1970 መከላከሉን ትገፋ የነበረው በፊት በነበሯት መሳሪያዎች ላይ ከዩጎዝላቪያና ቻይና የተገኙትን በመጨመር ነው፡፡ ሁለተኛው ስህተት ሶማሊያ የሶቪየት ህብረት አማካሪዎችን ያባረረችው በሀምሌ 1969 ነው የሚለው ነው፡፡ ይሁንና ነገሩ የተከሰተው በህዳር ወር 1970 ነው፡፡ በሶስተኛ ደረጃ የሶማሊያ ሰራዊት ጅጅጋን የያዘው በሀምሌ 1969 ሳይሆን መስከረም ወር 1970 መጀመሪያ ላይ ነው፡፡ ስለዚህ ለፈጸምኩት ስህተት ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ ለስህተቱ የዳረጉኝ በአማርኛ የተጻፉ ምንጮች ናቸው፡፡ በተለይም ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም የጻፉት መጽሐፍ ክስተቶችን በዝርዝር ከማስረዳቱ አንጻር ጥሩ የመረጃ ምንጭ ቢሆንም ብዙ የክሮኖሎጂ ስህተቶች (chronological errors) አሉት፡፡ ኮሎኔሉ በዚያን ጊዜ የያዟቸው የግል ማስታወሻዎችና ቃለ-ጉባኤዎች አሁን ስለሌላቸው ቀናትና ወራትን የዘነጓቸው ይመስለኛል፡፡ ===ሀረርን የመከላከል ውጊያ=== ከምስራቅና ደቡብ ኢትዮጵያ ከተሞች ሁሉ የሶማሊያ ጦር ከፍተኛ ትኩረት ያደረገው በሀረር ላይ ነው፡፡ ለዚህም ምክንያት አለው፡፡ ሀረር ረጅምና ጥንታዊ ታሪክ ያላት ከተማ በመሆኗ የሶማሊያ መሪዎች የኛ ከተማ ናት ይሏት ነበር፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ሀረር የዘመኑ ትልቁ የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገር የነበረው የሀረርጌ ዋና ከተማ ናት፡፡ በሶስተኛ ደረጃ ኢትዮጵያ ከነበሯት አራት ክፍለ ጦሮች መካከል በጣም ግዙፍ የሆነው የሶስተኛ ክፍለ ጦሮች ዋና የማዘዣ ጣቢያ የሚገኝባት ከተማ ነበረች፡፡ በአራተኛ ደረጃ ሀረር ብቸኛው የአትዮጵያ የጦር አካዳሚ የሚገኝባት ከተማ ናት፡፡ የሶማሊያ መሪዎች ይህንን ሁሉ በማመዛዘን ነው ሀረርን የትልቋ የድል ብስራት ማወጃ ማዕከል በማድረግ ያተኮሩባት፡፡ የሶማሊያ ጦር ሀረርን የመያዝ ጥረቱን የጀመረው በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ ነው፡፡ ውጊያውንም የጀመረው ከሀረር በ70 ኪሎሜትር (ከጅጅጋ በ40 ኪ.ሜ) ርቀት ላይ በምትገኘው የቆሬ ግንባር ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያኑ በዚህ ውጊያ ሲወጠሩ፣ የሶማሊያ ሰራዊት ከጭናክሰን ከተማ አቅራቢያ ተነስቶ በጉርሱም አውራጃ ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት በመራመድ የኤጀርሳ ጎሮ ከተማን ያዘ፡፡ በዚህም ሳያበቃ ሀይሉን ለሶስት በመክፈል አንደኛውን ቡድን በትንሿ የፈላና ከተማ ከተማ አቅጣጫ ወደ ሀረር ላከለው፡፡ ሁለተኛው ሀይል ከሀረር በስተሰሜን በመገስገስ የኮምቦልቻ ከተማን ከያዘ በኋላ ወደ ሀረር መግፋት ጀመረ፡፡ ሶስተኛው በአስደናቂ ፍጥነት ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ተጉዞ ከሀረር በስተምዕራብ ካለችው የአዴሌ ከተማ አጠገብ ደረሰ (የዚህኛው ግብረ-ሀይል ዓላማ የኢትዮጵያ ሰራዊት ከድሬ ዳዋ አቅጣጫ ድጋፍ እንዳይመጣለት መከላከል ነው)፡፡ የኢትዮጵያ ሰራዊት ሀረርን ላለማስነጠቅ ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረግ ጀመረ፡፡ ለውጊያው ከተሰለፈው ሀይል በተጨማሪ በተጠባባቂነት የተያዙ የመደበኛና የሚሊሻ ሰራዊት አባላት በሙሉ ሀረርን ለመከላከል እንዲሰማሩ ታዘዙ፡፡ ነገሮች ሁሉ እንዲህ በከረሩበት ጊዜ ደግሞ የሶማሊያ ሰራዊት አንድ ግብረ ሀይል ሌላ ያልታሰበ የውጊያ ግንባር ከፈተ፡፡ ይኸውም ሀይል የመጣው ከሀረር ከተማ በስተደቡብና በደቡብ ምዕራብ በኩል ነበር፡፡ በዚህ በኩል ወደ ሀረር የደረሰው የሶማሊያ ሰራዊት ከሁለት አካባቢዎች ነበር የተነሳው፡፡ የአንደኛው መነሻ በባሌ ክፍለ ሀገር የምትገኘው የኤል-ከሬ ከተማ ናት፡፡ ከዚያች ከተማ የተነሳ አንድ የሶማሊያ ብርጌድ ሽቅብ ወደ ላይ እየተጓዘ የዋቢ ሸበሌን ወንዝ በማቋረጥ ከሀረር ከተማ በደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ ከምትገኘው ትንሿ የ“ፊቅ” ከተማ ገባ፡፡ ሁለተኛው ሀይል ደግሞ በኦጋዴን ካለችው የደጋሀቡር ከተማ ከተነሳ በኋላ ወደ ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ እየገሰገሰ “ፊቅ” ከተማ ደረሰ፡፡ እነዚህ ሁለት ሀይሎች አንድ ላይ በመጣመር በቀድሞው የሀረር ዙሪያ አውራጃ ውስጥ ካለው የፈዲስ ወረዳ ከገቡ በኋላ ለሁለት ተከፈሉ፡፡ አንደኛው ሀይል የሰሜን ምስራቅ አቅጣጫን በመያዝ ሀረርን በደቡብ ምስራቅ የሚያዋስነውን የሀኪም ጋራ እንዲቆጣጠር ግዳጅ ተሰጠው፡፡ ሁለተኛው ሀይል ቀጥታ ወደ ሰሜን እየተጓዘ የሀረር ከተማ ምዕራባዊ ድንበር የሆነውን የአቦከር ተራራን እንዲይዝ ታዘዘ፡፡ የሶማሊያ ሀይሎች ፍጥነት በታየበት በዚህ ዘመቻቸው ሀረርን ሙሉ በሙሉ ለመክበብ ቻሉ፡፡ አልፎ ተርፎም በደቡብና በሰሜን በምዕራብ የመጡት ግብረ ሀይሎች መድፎቻቸውን የሀረር ከተማ ተጎራባች በሆኑት የአው ሀኪም እና የድሬ ጠያራ ቀበሌዎች ውስጥ በማስቀመጥ ከተማዋን መደብደብ ጀመሩ (ኮሎኔል መንግሥቱ በመጽሐፋቸው ገጽ 472 ላይ “የሶማሊያ ጦር ሀረርን ያዘ” ይላሉ፤ አንዳንድ ምንጮች ደግሞ “የሀረር ከተማ የተወሰኑ ክፍሎች በሶማሊያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር ወድቀው ነበር” በማለት ጽፈዋል፤ ይሁንና በሀረር ከተማ ቆይታዬ ያነጋገርኳቸው የከተማዋ ነዋሪዎችና የያኔው የኢትዮጵያ ሰራዊት አባላት የሀረር ከተማ በሶማሊ ሰራዊት እንዳልተያዘች አረጋግጠውልኛል፡፡ የሶማሊያ ሰራዊት ሀረርን ቢይዝ ኖሮ ከተማዋን ማስመለስም ሆነ ለቀጣዩ ጦርነት የኢትዮጵያን ሰራዊት ማደራጀት በጣም አስቸጋሪ ይሆን ነበር)፡፡ የሶማሊያ ጦር ከሀረር ከተማ በአራት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ደርሷል፡፡ ታዲያ ከተማዋን ለመያዝ ያልቻለበት ምክንያት ምንድነው? ሶስት ምክንያቶች አሉት፡፡ አንደኛው ኢትዮጵያ በስልጠና ላይ የነበረውን የሚሊሻ ጦር በከፊል አስመርቃ በውጊያው እንዲሳተፍ ለማድረግ መቻሏ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የነበሩትን የጦር ሀይሎች በፍጥነት አጓጉዞ በመከላከሉ ውጊያ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ መቻሉ ይጠቀሳል፡፡ ይሁንና እነዚህ ሁለት ምክንያቶች እንደ ደጋፊ ተደርገው ነው፡፡ ሀረርን በሶማሊያ ወራሪ ሰራዊት ከመወሰድ የዳነችበት ዋነኛ ምክንያት የኢትዮጵያ አየር ሀይል ያደረገው ተጋድሎ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር ሀይል በወቅቱ ጥቂት የጦር አውሮፕላኖች ናቸው የነበሩት፡፡ ከሶቪየት የተገኙት አውሮፕላኖችም በዚያን ጊዜ ወደ ሀገር ቤት አልገቡም፡፡ ነገር ግን የአየር ሀይሉ አብራሪዎች በጣም የተዋጣላቸው በመሆናቸው ዒላማቸውን ሳይስቱ ይመቱ ነበር፡፡ በድሬ ዳዋ (ጀልዴሳ) ግንባር በርካታ ታንኮችን ከጥቅም ውጪ እንዳደረጉት ሁሉ በዚህም ግንባር የሶማሊያ መድፎችንና ሞርታሮችን በመደምሰስ ከዒላማቸው አሰናክለዋል፡፡ ታዋቂው የኢትዮጵያ አየር ሀይል አብራሪና የህብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሜዳይ ተሸላሚ ብርጋዴር ጄኔራል ለገሰ ተፈራ ብቃቱን ካሳየባቸው ግዳጆች አንዱ ያ ሀረርን ለመከላከል የተደረገው ውጊያ ነው፡፡ (በነገራችን ላይ የሶማሊያ ሰራዊት ሀረርን ለመያዝ በተደረገው ዘመቻ መድፍና ቢ ኤም እንጂ ታንክ መጠቀሙ አልተዘገበም)፡፡ === የሶቪየት-ኩባ-ደቡብ የመን አጋርነት ለኢትዮጵያ=== ነሀሴ ወር 1970፡፡ ሶቪየት ህብረት ለመጨረሻ ጊዜ ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬን ወደ ሞስኮ ጠራቻቸው፡፡ በሀይል የያዙትን የኦጋዴንን ግዛት እንዲለቁ እና ጉዳዩን በሰላም እንዲጨርሱም መከረቻቸው፡፡ ፕሬዚዳንት ዚያድ ግን በእምቢታቸው ጸኑ፡፡ በዚህም የተነሳ ታላቋ ሶቪየት ህብረት ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ ጀመረች፡፡ ቀደም ሲል በተስማማችው መሰረት በመስከረም ወር 1970 ለኢትዮጵያ የ385 ሚሊዮን ዶላር መሳሪያ የሚሸጥበትን ሂደት ገቢራዊ ማድረግ ጀመረች፡፡ በመርከቦቿ ወደ ሶማሊያ ነዳጅ ማጓጓዙን አቋረጠች፡፡ ለሶማሊያ የምታደርገውን የጦር መሳሪያ ሽያጭ አቆመች፡፡ ሶማሊያ በህዳር ወር 1970 በሀገሯ የነበሩትን የሶቪየት አማካሪዎች ስታባርር ሶቪየት ህብረት “ወራሪ” በማለት አወገዘቻት፡፡ ወረራውን ለመቀልበስ ከኢትዮጵያ ጋር በሙሉ ፍላጎት እንደምትሰራም አስታወቀች፡፡ በዚህም መሰረት እንደ እርሷ ሁሉ የኢትዮ-ሶማሊያ ውዝግብን በሰላም ለመቋጨት ጥረት ሲያደርጉ የነበሩትን ኩባና ደቡብ የመንን የሚያካትት ወታደራዊ “አክሲስ” ተመሰረተ፡፡ የዚህ አክሲስ ተግባር ከኢትዮጵያ ሰራዊት ጋር በመቀናጀት የሶማሊያ ሰራዊትን ማባረር ነው፡፡ ሶስቱ ሀገራት በጦርነቱ የነበራቸው ተሳትፎ ሲጠቃለል የሚከተለውን ይመስላል፡፡ ሀ/. የሶቪየት ህብረት ተሳትፎ ሶቪየት ህብረት የምድር ጦር ሀይሏ ምክትል አዛዥ የነበሩትን ሜጀር ጄኔራል ቫሰሊ ፔትሮቭን የዓለም አቀፉ ቡድን ሃላፊ አድርጋ መድባለች፡፡ የጄኔራሉ ሃላፊነት የኢትዮጵያን ሰራዊት ማማከርና በኢትዮጵያ መሪዎችና ሞስኮ በሚገኘው የሶቪየት ህብረት የጦር ሀይሎች ጠቅላይ መምሪያ መካከል እንደ አገናኝ ሆኖ ማገልገል ነው፡፡ ከጄኔራል ፔትሮቭ በተጨማሪ ሶቪየት ህብረት • በክፍለ ጦርና በብርጌድ ደረጃ የሚያገለግሉ የጦር አማካሪዎችን መድባለች፡፡ • የከባድ መሳሪያና በረራ አሰልጣኞችን አስመጥታለች፡፡ • የሶማሊያ የጦር ሀይል ክምችትና የስምሪት አቅጣጫዎችን የሚያሳዩ የጦር መረጃዎችን (ስታቲስቲክስ፣ ካርታ ወዘተ) ለኢትዮጵያ ሰጥታለች፡፡ • ለጦር ቁስለኞች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታና የቀዶ ጥገና ህክምና የሚሰጡ ሀኪሞችን መድባለች፡፡ ከዚህ ሌላ ሶቪየት ህብረት በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ አጋር ሆና ቆይታለች፡፡ ሆኖም ሶቪየቶች ድጋፍ ሰጪ ከመሆን ባሻገር ተዋጊ የጦር ሀይል አልመደቡም፡፡ ለ./. ኩባ በቆዳ ስፋቷ ትንሽ የሆነችው የኩባ ሶሻሊስት ሪፐብሊክ በጦርነቱ ሂደት በቀጥታ ከተሳተፉት ሁለት ሀገራት አንዷ ናት፡፡ በወቅቱ ኩባ ያስመጣችው የተዋጊ ብዛት ከ16, 000 እስከ 20, 000 ይገመታል፡፡ ከዚህ ሀይል መካከል ሁለቱ ሜካናይዝ ብርጌድ ነው፡፡ ወደ የመጣው ኢትዮጵያ የኩባ ጦር የሚመራው የሀሪቱ ም/የመከላከያ ሚኒስትር በነበሩት በጄኔራል አርናልዶ ኦቾዋ ሲሆን በዘመኑ በአንጎላ ተመድቦ የነበረውንም የኩባ የጦር ሀይል የሚያዘው እርሱ ነው፡፡ ሐ/. ደቡብ የመን ደቡብ የመን ለጦርነቱ የመደበችው 2000 መድፈኞችን ነው፡፡ እነዚያ መድፈኛ የመኒዎች በቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆኑም አልሞ-ተኳሽ መሆናቸው በብዙዎች ዘንድ ተደንቆላቸዋል፡፡ ----- ሶስቱ ሀገራት ለረጅም ጊዜ የሶማሊያ አጋር ነበሩ፡፡ ሶማሊያ የመሬት ጥያቄዋን ባነሳችበት ጊዜም ሀሳቧን እንድትቀይር ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ ከዚህም አልፎ ፕሬዚዳንት ካስትሮ “ሶማሊያ፣ ኢትዮጵያና ደቡብ የመን በኮንፌዴሬሽን ተያይዘው አንድ ታላቅ ህብረት መመስረት አለባቸው” የሚል ሃሳብ እስከ ማቀንቀን ደርሰዋል፡፡ ----- ባለፈው ክፍል እንደገለጽኩት ሌሎች የሶሻሊስት ሀገራት በጦርነቱ ሂደት በቀጥታ ባይሳተፉም ለኢትዮጵያ የመሳሪያ ድጋፍ አበርክተዋል፡፡ ሶማሊያ በግልጽ ሶሻሊዝምን ወርውራ ወደ ምዕራቡ ዓለም መጓዝ የጀመረችው በዚያን ጊዜ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ቀደም ብሎም ቢሆን ከምዕራባዊያን ጋር ድብቅ ግንኙነቶችን ማድረግ እንደ ጀመረች አንዳንድ ምንጮች ያወሳሉ፡፡ ለምሳሌ ከአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ጋር ቁርኝት ካለው አንድ ተቋም የተገኘ ጥናታዊ ጽሑፍ አሜሪካ፣ ብሪታኒያ እና ፈረንሳይ ለሶማሊያ የጦር መሳሪያዎችን ለመሸጥ በድብቅ የተስማሙት ወረራው በተጀመረበት የሀምሌ ወር (1969) መሆኑን ይገልጻል፡፡ ከዐረብ ሊግ ሀገራት መካከል ግብጽና ሳዑዲ ዐረቢያ በድብቅ ሶማሊያን ይረዷት ነበር፡፡ ሊቢያ ግን የኢትዮጵያ ደጋፊ ነበረች፡፡ ----- (ይቀጥላል) ሚያዚያ 8/2006 ተጻፈ፡፡ ------ ጠቃሚ የመረጃ ምንጮች 1. Evil Days, Thirty Years of War and Famine in Ethiopia: An Africa Watch Report, New York , September 1991 2. Gebru Tareke, “The Ethiopia-Somalia War of 1977 Revisited, Journal of African Historical Studies, pp-635-667 3. Gebru Tareke, The Ethiopian Revolution: War in the Horn of Africa, New Haven CT, Yale University Press, 2009 4. Kenneth G. Weiss, “The Soviet Involvement in the Ogaden War”, Center for Naval Analysis, Alexandria, Virginia, February 1980 5. Mesfin Wolde-Mariam: Somalia A Problem Child of Africa, 1978 6. Tibebe Eshete, The Root Cause of Ogadeni Problem, Journal of North African Studies, Vol 13, Number 1, 1991 7. ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም፣ “ትግላችን”-የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ የትግል ታሪክ፡ ጸሐይ አሳታሚና አከፋፋይ ድርጅት፡ ሎስ አንጀለስ 2004 8. ብ/ጄኔራል ካሳዬ ጨመዳ፤ የጦር ሜዳ ውሎዎች ከምስራቅ እስከ ሰሜን፡ አዲስ አበባ፣ 2000 9. ብ/ጄኔራል ተስፋዬ ሀብተማሪያም፣ የጦር ሜዳ ውሎ፣ አዲስ አበባ፣ 1996 10. ዘነበ ፈለቀ፣ “ነበር”፣ አዲስ አበባ፣ 1996 11. ገነት አየለ አንበሴ፣ የሌ/ኮ/ መንግሥቱ ኃይለማሪያም ትዝታዎች፣ ሜጋ አሳታሚ ድርጅት፣ 1994 ------ The writer, Afendi Muteki, is a researcher and author of the ethnography and history of the peoples of East Ethiopia. You may like his facebook page and stay in touch with his articles and analysis: Just click the following link to go to his page. https://facebook/afendimutekiharar
Posted on: Sun, 12 Oct 2014 14:30:31 +0000

Trending Topics



Recently Viewed Topics




© 2015