‹‹ደህና ሰው ሲበላሽ ቅራሬ የለውም›› - TopicsExpress



          

‹‹ደህና ሰው ሲበላሽ ቅራሬ የለውም›› ------------------------------------------------------------------------- ወይኔ አመብርሃን! እኔና ቃልአብ የዘጠንኛ ሲ ን በር ዘግተን ስንሳሳም ዩኒት ሊደሩ ያዘን፡፡ ሰአቱ የከሰአት ተማሪ ሁሉ ጥርግርግ ብሎ የወጣበት እና ግቢው ጭር እረጭ የሚልበት ስለነበር፤ በሰላም ለመሳሳም ነበር ሃሳባችን፡፡ ዩኒት ሊደራችን ‹‹ጅቦ›› ግን ማን ይንገረው ወይ ይሄ የጅብ አፍንጫው ምን ያሽተተው አላውቅም፤ በሩን ብርግድ አድርጎ ስንሳሳም ደረሰብን፡፡ እመብርሃንን! ቃልአብዬ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ላይብረሪው የሚወስደው ጨለማ ኮሪደር ላይ ሰርቆ ከሳመኝ ወዲህ ለምንም ለማንም እንዲህ ደንግጬ አላውቅም፡፡ ያኔ መደንገጤ ሲያንስ ነው፡፡ የአስቴር ሙዚቃ ሳይከፈት፣ ለስላሳ ሳልጋበዝ፣ ሳልቅለሰለስ፣ ሳልሽኮረመም፣ ‹‹ሒድ ከዚህ አንተ…ምን አይነቱ ነው?..›› ብዬ ሳልግደረደር፣ እንደው ያለማስጠንቀቂያ በድንግዝግዝ የላይብረሪ ኮሪደር ላይ፤ ያውም ሰው ውር ውር በሚልበት ቦታ ላይ፤ ከንፈሬን በድንገት ስሰረቅ መደንገጥ ይነሰኝ…!? ደሞ ምናለ እስቲ አይኔን በትንሹ እንኳን ከፍቼው ቢሆን ኖሮ… ቢያንስ ጅቦ በሩን መክፈት ሲጀምር እደርስበት ነበር፡፡ ‹‹ዝም ብለን እያወራን እኮ ነው›› ለሚል ደረቅ ውሸት ጊዜ እገዛ ነበር፡፡ ከዚህ ቅሌት እድን ነበር፡፡ ከቃልአብ ጋር መሳሳም የጀመርን ሰሞን እንደ አሻንጉሊት አይኖቼን ከፍቼ ነበር የምሳተፈው፡፡ እግዜር ይይላትና ያቺ ቁሌታም ሉሊት ናት ጉድ የሰራችኝ… ‹‹እንዴ…!ሁለቱንም አይንሽን ካልጨፈንሽ እኮ ምንም ደስ አይልም…ካላመንሽ አካፑልኮ ላይ ቶኒና ሬቼል ሲሳሳሙ እዬ…!ሙች…ጨፍነሽ ሞክሪው›› ብላ እንዲህ ያለማስጠንቀቂያ እንድያዝ አደረገችኝ፡፡ ለቅሌት ወጥመድ ዳረገችኝ፡፡ እኔ ሬቼል አይደለሁ፡፡ ቃልአብ ቶኒ አይደል፡፡ ምናለ ዝም ብዬ አይኔን ከፍቼ ብሳምስ ኖሮ፡፡ እኛ ሆዬ እንደነቶኒ አይናችንን ድብን አድረገን ጨፍነን ስንላላስ ፤በአለም ላይ ከሁለታችን ውጪ ሰው መኖሩን ያወቅነው ይሄ ጅቦ በጅብ ድምፁ፤ ‹‹ጉድነስ ኢን ሄቨን!›› ሲል ነበር፡፡ ‹‹ጉድነስ ኢን ሄቨን!›› ጅቦ ፤ ቾክ እጁን ሲያበላሸውም፣ ወረቀት ከእጁ ሲያመልጠውም፣ እንቅፋት ሲመታውም፣ ፣ ተማሪ የተሳሳተ መልስ ሲሰጥም፣ ስንረብሽም፣ የትም የሚሰካት ቃሉ ናት፡፡ ዛሬ ስሳሳም አግኝቶኝም እንዲህ ይበለኝ እንጂ ፤ ጎበዝ ተማሪ ስለነበርኩ ከሴክሽኖች ሁሉ አንደኛ ወጥቼ ስሜ ሲጠራም ‹‹ጉድነስ ኢን ሄቨን!›› ብሎ ነበር የጨበጠኝ፡፡ ቃልአብ ቀ…ስ ብሎ እጆቹን ከሸሚዜ ስር አወጣ፡፡ ጉዳያችን ከከንፈር እየወረደ ነበር፡፡ እኔ ደንዝዤና አቀርቅሬ የተፈጠረውን ነገር ለመረዳት ዴስክ ዴስኩን ማየት ጀመርኩ፡፡ ይህ ዴስክ፤ የክፍል ስራ ከሁሉ ተማሪ ቀድሜ ጨርሼ ‹‹ራይት በራይት›› አግኝቼ ስመለስ የተፃፈውን ‹‹እ.በ.ጥ›› ወይ ‹፣ኤክሰለንት›› የሚለውን የአስተማሪዎቼን ፅሁፍ በኩራት ደጋግሜ ለማየት ደብተሬን የማስቀምጥበት እንጂ በሃፍረት የምደገፈው.፣ አቀርቅሬ የማየው አልነበረም፡፡ አፈርኩ፡፡ ክፉኛ አፈርኩ፡፡ ‹‹ና ውጣ አንተ!...ዱርዬ…ውጣ አልኩህ እኮ!›› ባላሰብኩት ፍጥነት ቃልአብን የሸሚዙ ኮሌታ ጋር ጭምድድ አድርጎ ይዞ ከዴስኩም፣ ከግድግዳውም ጋር እያጋጨ ከክፍል አስወጣው፡፡ የሚሆነውን አያለሁ ግን መንቀሳቀስ አልቻልኩም፡፡ ከወንበሩ የተሰፋሁ ይመስል ቁ…ጭ እንዳልኩ ቀረሁ፡፡ ሳይቆይ ጅቦ ተመልሶ መጣ፡፡ ‹‹ሴት ተማሪዎችን ሳይቀር በጥፊ ይማታል›› ሲባል ስለሰማሁ እምባ እምባ አለኝ፡፡ በ‹‹የሚኮራብኝን አስተማሪዬን አሳዘንኩት›› ሃፍረት ራሴን ብቀጣም ‹‹ቲቸር አይለመደኝም›› የሚል ቃል ማውጣት ግን አልቻልኩም፡፡ ረጅም እና ወደጎን ብዙ የሆነ ሰውነቱን ይዞ ወደ ተቀመጥኩበት ዴስክ መጣ፡፡ ‹‹ካሁን ካሁን አጣፈረኝ፣ ካሁን ካሁን አጮለኝ›› ስል ‹‹ሸሚዝሽን በስነስርአት ቆልፊ›› አለኝ በዛው የጅብ ድምፁ፡፡ የትላልቅ ጡቶቼ ሶሰት አራተኛ ውጪ እንደነበር የታወቀኝ ያኔ ነው፡፡ ገፋፍቼ ቦታቸው ከመለስኳቸው በኋላ ለጥፊው ተዘጋጀሁ፡፡ ‹‹ካንቺ ይሄን አልጠብቅም ነበር፡፡ መቼም ደህና ሰው ሲበላሽ ቅራሬ የለውም..በይ አሁን ወደ ቤትሽ ሂጂ›› ብሎኝ ወጣ፡፡ ጥፊ ጠብቄ ስለነበር ባለመመታቴ ልደሰት ይገባ ነበር፡፡ ግን አልተደሰትኩም፡፡ ንግግሩ እና አነጋገሩ ከጥፊም፣ ከቡጢም በላይ አመመኝ፡፡ ጅቦ አልተናደደብኝም፡፡ ጅቦ ተቀይሞኛል፡፡ ጅቦ አዝኖብኛል፡፡ ቤት ገብቼ ምሽቱን ሙሉ ‹‹ደህና ሰው ሲበላሽ ቅራሬ የለውም›› ያለውን ሳመነዥክ አደርኩ፡፡ ለወትሮም ከመሳሳም ውሎዬ በኋላ ስለቃልአብ የማስብበት መደበኛ ሰአቴ ሲያልቅ የማመሸው ከደብተሬ ጋር ስለነበር ሚጢጢዋ ሳሎናችን ውስጥ ተጠጋግተው ያሉት አናቴም፣ አባቴም፣ ሁለቱ ወንድሞቼም፣፣ የአክስቴ ልጅም ግራ ተጋብተው እያዩኝ ነበር፡፡ ነገሩ ቢገባኝም ለማረጋገጥ እናቴ አጠገብ ሄጄ፤ ‹‹አማ፤ ደህና ሰው ሲበላሽ ቅራሬ የለውም ማለት ምን ማለት ነው?›› ብዬ ጠየቅኳት፡፡ እናቴ የተረትና ምሳሌ፣ የምሳሌያዊ አነጋገር ንግስት ናት፡፡ ‹‹ጠይቋችሁ ነው?›› አለችኝ፡፡ ‹‹ማን?›› ‹‹አስተማሪ ነዋ! ምን ማለት ነው ተብላችሁ ተጠይቀችሁ ነው?›› ‹‹እ..አዎ፡፡ ምን ማለት ነው…?›› ‹‹ያው ደህና ሰው ከተበላሸ መመለሻም የለው ማለት ነው፡፡ ሙሉ በሙሉ ይጠፋል እንደማለት ነው፡፡…ጥሩ ምክር ያለው ነገር ያስተምራሉ ማለት ነው፡፡ ጥሩ ነው›› አልቅሽ አልቅሽ አለኝ፡፡ ‹‹እማ…?>> ‹‹እ…?.›› ‹‹እውነት ነው ግን?›› አልኳት በልቤ እያልኩ :: ‹‹ምኑ?›› ‹‹ደህና ሰው ከተበላሸ አይመለስም ያልሽው›› ‹‹እህስ…ነው እንጂ፡፡ ቅራሪ የለውም ያሉት እኮ ለዚህ ነው፡፡ ያለ ምክንያት መስሎሽ ነው…›› በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ጅቦ የዘጠንኛ ሲን በር ዘግቼ በምስጢር ያደረግኩትን ለአስተማሪዎቸ ሁሉ ነገሮብኝ ከሚከተሉት ምላሾች የተነሳ ስሰቃይ ከረምኩ፡፡ አማርኛ አስተማሪዬ፤ ‹‹የት ይደርሳል የተባለ በሬ ሉካንዳ ቤት ተገኘ አሉ›› በየጊዜው ፈተና በመድፈኔ የሚኩራራብኝ የሂሳብ አስተማሪዬ፤ ‹‹ ጎበዝ ተማሪ ሆነሽ ሳለ ይህን ማመዛዘን አለመቻልሽ ያሳዝናል…የሂሳብ ትምህርት ካሰላው ጭንቅላት ይህን አልጠብቅም ነበር›› ግብረገብ አስተማሪዬ፤ ‹‹ጉብዝና ያለ ግብረገብ የትም አያደርስም›› ሽማግሌው የባይሎጂ አስተማሪዬ፤ ‹‹እኛ በቲዎሪ ልጆቹ እንዳይበላሹ እያልን ስንሳቀቅ የምናስተምረውን አጅሪት በተግባር አደረግሽው አሉ! ወይ የዛሬ ልጆች!›› ሌላው ቀርቶ ወጣቷ የሲቪክስ መምህሬ እንኳን ‹‹አድገሽ የመጀመሪያዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ወይ የሆነ ትልቅ ሀገር አምባሳደር ትሆኛለሽ ብለን ስናስብ የዱርዬ ለምቦጭ ላይ ተለጥፈሽ ትገኛለሽ? I am terribly disappointed ›› ስትለኝ ፤ ላልገኝ የጠፋሁ፣ ላልገጣጠም የተሰባበርኩ፣ ላልጠራ የደፈረስኩ፣ ላልነሳ የወደቅኩ መሰለኝ፡፡ ይባስ ብሎ በሊቀመንበርነት እመራው የነበረው የተማሪዎች ፀረ ኤች አይ ቪ ክበብ ‹‹ያሳየሽው ባህሪ ከክበቡ አለማ ጋር ስለሚፃረር በአባልነት መቀጠል እንደማትችይ ተወስኗል›› ብሎ አባረረኝ፡፡ ያኔ በይፋ መበላሸቴን ተረዳሁ፡፡ ያኔ እኔም እንደሁሉም፤ እየተሳሳሙ ጎበዝ ተማሪ መሆን እንደማይቻል ተረድቼ፣ አንዱን ጎዳና መምረጥ እንዳለብኝ አገናዝቤ፣ ‹‹ከፀፀተሽ ይቅር በቃ ተመለሽ›› የሚለኝ እንደሌለ አውቄ፤ ‹‹ደህና ሰው ሲበላሽ ቅራሬ የለውም›› አልኩና ትምህርትና ትምህርት ትምህርት ከሚሸት ነገር ሁሉ አጥብቄ ሸሸሁ፡፡ በ‹‹ካፈርኩ አይመልሰኝ››፣ከቃልአብና እንደ ቃልአብ ከሚስሙ ወንዶች ተጠጋሁ፡፡ ‹‹ደህና ሰው ከተበላሸ መመለሻም የለው›› ብዬ፤ መያዝን ሳልፈራ፣ ቁጣና ጥፊን ሳልፈራ፣ መደንገጥን ሳልፈራ፤ በጠራራ ፀሃይ፣ በሰው ጅረት መሃል፣ እንደ አካፑልኮዋ ሬቼል ሁለቱም አይኖቼን ግጥም አድርጌ ጨፍኜ መሳምን ኑሮዬ አደረግሁ፡፡
Posted on: Mon, 21 Oct 2013 02:48:36 +0000

Trending Topics



Recently Viewed Topics




© 2015