ጥናት 19 (ኤፌሶን 5፣8-20) በብርሃንና - TopicsExpress



          

ጥናት 19 (ኤፌሶን 5፣8-20) በብርሃንና በጥበብ መመላለስ ---------------------------------------- 1)በብርሃን መመላለስ ቁ. 8-14 ሀ)የብርሃንና የጨለማ ትርጉም:- በዚህ ክፍል ብርሃንና ጨለማ የሚሉትን ቃላትን ሲጠቀም ጳውሎስ ምን ሊል እንደፈለገ ለመረዳት ቁ. 9 እና 11ን በጥንቃቄ ማንበብ ያስፈልጋል:: “የብርሃኑ ፍሬ በበጎነትና በጽድቅ በእውነትም ሁሉ ነውና...” ቁ. 9:: ብርሃን መሆን ማለት እንግዲህ እንዲሁ የማይታይና የማይጨበጥ መንፈሳዊ ነገር ሳይሆን፣ መልካም ፍሬ ያለው በመልካም ሥራና አኗኗር የሚገለጥ ሕይወት ነው:: “ፍሬም ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ” ቁ. 11:: ጳውሎስ ስለ ጨለማ ሲናገርም እንዲሁ የማይጨበጥና የማይታይ ነገር አድርጎ ሳይሆን የሚገልጸው፣ ይልቁንም ፍሬ ቢስ በሆነ ሥራ የሚገለጥ እንደሆነ ነው የሚያሳየን:: ስለዚህ በዚህ ክፍል ብርሃንና ጨለማ ሲል ለዘላለም ሕይወት መልካም ፍሬን ስለሚያፈራ በአኗኗር ስለሚታይ ሕይወትና በተቃራኒው ከጉዳት በስተቀር ጥቅም ወይም ፍሬ የሌለውን ክፉ ሥራ የሚያመለክት ነው:: ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ላይም እንዲሁ ስለ ጨለማ ሥራ ሲናገር፣ እግዚአብሔርን ደስ የማያሰኝን የኃጢአትን ኑሮ ለማመልከት ነው:: “ሌሊቱ አልፎአል፣ ቀኑም ቀርቦአል:: እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ:: በቀን እንደሚሆን በአገባብ እንመላለስ፣ በዘፈንና በስካር አይሁን፣ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፣ በክርክርና በቅናት አይሁን፣ ነገር ግን ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፣ ምኞቱንም እንዲፈጽም ለሥጋ አታስቡ::” ሮሜ 13፣12-14:: ጌታም አማኞች የዓለም ብርሃን እንደሆኑ ተናግሮአል:: “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ::” ማቴ 5፣14:: ጌታም እንዲሁ ብርሃን ናችሁ ሲል ልዩና ምስጢራው ስለሆነና ስለማይገባ መንፈሳዊ ነገር ለመናገር ፈልጎ ሳይሆን በመልካም ሥራ የሚገለጥን ሕይወት ለማመልከት ነው:: “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ::” ማቴ 5፣16:: ስለዚህ ጳውሎስ እናንተ ጨለማ ነበራችሁ ሲል እግዚአብሔርን ደስ የማያሰኝን ነገር እያደረጋችሁ በኃጢአት የምትኖሩ ሰዎች ነበራችሁ ለማለት ነው:: እንዲሁም አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ ሲል፣ ከጌታ የተነሣ አሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና መልካም ፍሬን የሚያፈራ ሕይወት አላችሁ ማለት ነው:: ለ)የብሃንና የጨለማ ባሕርያት:- መጽሐፍ ቅዱስ ለምን በጌታ የሆኑትን ብርሃን፣ ያላመኑትን ደግሞ እንደ ጨለማ አድርጎ ይጠራቸዋል? የብርሃንና የጨለማን አንዳንድ ባሕርያት በቅርበት ስንመለከት፣ ለምን መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ነገሮች እንደ ምሳሌነት እንደተጠቀመባቸው የበለጠ ግልጽ ይሆንልናል:: ብርሃንና ጨለማ ኮንትራስቶችና ተቃራኒዎች ናቸው:: አንዱ ባለበት ሌላኛው አይኖርም፣ ጎን ለጎንም በአንድነት አብረው አይገኙም፣ አብሮ ለመኖር አያመቻምቹም/compromise ወይም አይስማሙም፣ በአንዱ እግር ሌላው ይገባል፣ ከሁለቱ ውጭ የሆነ የተለየ መሃል ሰፋሪ የሆነ ቦታም የለም:: ይህም ማለት ብርሃን ሲበራ ጨለማ ወዲያው ሥፍራውን ለብርሃን ይለቅቃል፣ ብርሃንም ጨለማም አብረው እየተስማሙ የሚኖሩበት ቦታና ጊዜ የለም፣ ልክ ብርሃን ስፍራውን ሲለቅቅ ወዲያው ጨለማ በእግሩ ይተካል:: ስለዚህ አብሮ ለመኖር ጨርሶ ሕብረትና ስምምነት የማያደርጉ ነገሮች ናቸው:: “...ብርሃን ከጨለማ ጋር ምን ሕብረት አለው?” 2ቆሮ 6፣14:: እነዚህ ምሳሌዎች በዚህ በምናጠናው ክፍል በጌታ ያገኘነውን አዲሱን ሕይወትና የቀድሞውን በዓለም የነበረንን ኑሮ የሚያመለክቱ ናቸው:: “ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁና፣ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ” ቁ. 8:: ስለዚህ ከቀድሞ ኑሮአችን የአሁኑ በጌታ ያለን ሕይወት ምን ያህል ተቃራኒና የተለየ ሊሆን እንደሚገባው በዚህ ጳውሎስ ያሳስበናል:: ጨለማ ድብቅ ሥራንም ያመለክታል፣ በእግዚአብሔር ፊት ሊደረግ የማይቻልን ስለዚህም ተደብቆና ከእግዚአብሔር ርቆ የሚደረግን ሥራ ወይም በእግዚአብሔር አይን ሲታይ ነውር የሆነን ሥራ ሁሉ የሚያመለክት ነው:: “እነርሱ በስውር ስለሚያደርጉት መናገር እንኳ ነውር ነውና” ቁ. 12:: ስለዚህ የጨለማ ሥራ ስውርና ነውር የሆነ ሥራንም ያመለክታል:: በተቃራኒው ብርሃን ግን በእግዚአብሔር ፊት ያለምንም ችግር የሚደረግ፣ ጌታ የማያዝንበት፣ ነውር ያልሆነና የሚታይ ነው:: “ሁሉ ግን በብርሃን ሲገለጥ ይታያል፣ የሚታየው ሁሉ ብርሃን ነውና::” ቁ. 13:: “ብርሃንም ወደ ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ ፍርዱ ይህ ነው:: ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፣ እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደ ሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል::” ዮሐ 3፣19-21:: ሐ)እንደ ብርሃን ልጆች መመላለስ በተግባር ሲተረጎም:- እንደ ብርሃን ልጆች ወይም በብርሃን መመላለስ ማለት በተግባር ሲተረጎም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና መልካም ፍሬ ያለው ሕይወት መኖር ማለት ነው:: ጳውሎስ ብርሃን የሆነ ሕይወት በተግባር ምን ማለት እንደሆነ ሲገልጽ፣ የሚከተሉትን መግለጫዎች በመስጠት ነው:- · የብርሃን ፍሬ ያለው ሕይወት ከላይ ቀደም ብለን እንደገለጽነው በዚህ የጥናታችን ክፍል አገላለጽ ብርሃን መልካምና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕይወትን የሚያመለክት ነው:: የብርሃን ፍሬ ተብለው በዚህ ክፍል የሚከተሉት ሶስት የሕይወት ባሕርያት ተጠቅሰዋል:- · በጎነት:- kindly goodness ማለትም ደግነት፣ መልካምነት ወይም የክፋት ተቃራኒ · ጽድቅ:- መጽድቅ (በህብራይስጥ Sadaq) የሚለው ቃል የፍርድ ቤት ህጋዊ ሂደቶችን የሚያመለክት ቃል ነው:: መሠረታዊ ትርጉሙም በፍርድ ሂደት ውስጥ አንድ ሰው በሚከሰስበት ጉዳይ ከበደል ወይም ከጥፋት ነጻ መሆኑን የሚገልጽ ነው:: “ነገሬን ተግታችሁ ስሙ፣ ምስክርነቴንም በጆሮአችሁ አድምጡ:: እነሆ፣ ሙግቴን አዘጋጃለሁ:: እንደምጸድቅም አውቃለሁ::” ኢዮብ 13፣17-18 ኢዮብ ጓደኞቹ ጉዳዩን በደንብ አድምጠው፣ ምስክርነቱንም ሁሉ አጢነው እንዲፈርዱለትና በመጨረሻም በዚህ ጉዳይ አላጠፋህም ወይም ጻድቅ ነህ እንዲሉት ሲያሳስባቸው እንመለከታለን:: በመጽሐፍ ቅዱስ እንደምነመለከተው መጽደቅ በፍርድ ሂደት በአንድ በተውሰነ ጉዳይ በደለኛ አለመሆንን የሚያመለክት ነው:: “በሰዎች መካከል ጠብ ቢሆን፣ ወደ ፍርድም ቢመጡ፣ ፈራጆችም ቢፈርዱባቸው፣ ጻድቁን ደህና ነህ፣ የበደለውንም በደለኛ ነህ ይበሉአቸው::” ዘዳግም 24፣1 በዚም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የምንመለከተው ሁለት ሰዎች በአንድ ጉዳይ ላይ ቢካሰሱና ቢጣሉ ፈራጆች ምን ማድረግ እንደሚገባቸው ነው:: ጉዳዩን መርምረው በጉዳዩ ጥፋት የሌለበትንና በደለኛውን በግልጽ እንዲለዩ እግዚአብሔር ሲያዛቸው እናያለን:: በክፍሉ ውስጥ እንደምናነብበው፣ በጉዳዩ ጥፋት ያልተገኘበት ሰው ጻድቁ ተብሎ ሲጠራ እናያለን:: ይህ ማለት ሰውዬው ሁልጊዜ ስህተት የማይገኝበት ፍጹም ነው ለማለት ሳይሆን፣ በጉዳዩ ከበደል ነጻ መሆኑንና ጥፋተኛ አለመሆኑን ለማሳየት ነው:: በምንባቡ ያልበደለውን ወይም ጻድቁን ደህና ነህ ይበሉት በሚለው አባባል፣ በአማርኛ ደህና ነህ ተብሎ የተተረጎመው ቃል በህብራይስጡ Sadaq የሚለው ቃል ነው:: በሌላ አነጋገር ጻድቁን ጻድቅ ነህ በደለኛውንም በደለኛ ነህ ይበሉአቸው፣ የሚለውን ትርጉም ይይዛል ማለት ነው:: ስለዚህ መጽደቅ የሚለው ቃል ጥፋተኛ ወይም በደለኛ አለመሆንን ከዚህም የተነሳ ከፍርድ ነጻ መሆንን የሚያሳይ ቃል ነው:: እንዲሁም ጻድቅ የሚለው ቃል እንደዚህ በደል ያልተገኘበትን ሰው የሚያመለክት ነው:: ለምሣሌ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ጻድቅ እንደሆነ ይነግረናል:: ይህም ማለት ሥራውና ድርጊቱ በደልና ስህተት እንደማይገኝበት ለመግለጽ ነው:: ከዚህ በተጨማሪም ጽድቅ ከበደልና ከስህተት የራቀን መልካም ሥራንም የሚያመለክት ነው:: “ጽድቄን እይዛለሁ እርሱንም አልተውም...” ኢዮብ 27፣6 ኢዮብ በዚህ ክፍል ከበደልና ከክፋት የራቀ መልካም ሥራውን ጽድቄ ብሎ ይጠራዋል:: ይህም ማለት ትክክል የሆነና በፍርድም ቦታ ቢመረመር ጥፋት አላደረግህም፣ ትክክል አድርገሃል ወይም ጻድቅ ነህ የሚያስብል መልካም ሥራ ማለት ነው:: እንግዲህ ለማጠቃለል፣ መጽደቅ በፍርድ ቤት ታይቶና ተመርምሮ ከበደል ነጻ መሆነን ያመለክታል:: እንደዝህ ፍርድ ቤት ነጻ የሚያውጣው ሰው ደግሞ ጻድቅ ተብሎ ሲጠራ፣ ለዚያ ያበቃው ከክስህተት የራቀው ሥራው ደግሞ የሰውዬው ጽድቅ ይባላል ማለት ነው:: ስለዚህ እንደዚህ እንደ ጥናታችን ክፍል፣ ጽድቅ ማለት እግዚአብሔር ሊቀበለው የሚችለው ሕይወት ወይም በእግዚአብሔር ፍርድ ወይም አይን ሲታይ መልካም የሆነ ኑሮን ያመለክታል ማለት ነው:: ይህም የኃጢአትና የበደለኛ ሕይወት ተቃራኒ ነው:: · እውነት:- እውነተኝነት ወይም የሐሰተኛና የውሸት ተቃራኒ · ጌታን ደስ የሚያሰኝ ሕይወት እንደ ብርሃን ልጆች መመላለስ ሌላው ገጽታው በምናደርገንው ድርጊት ሁሉ ከማድረጋችን በፊት ይህ ጌታን ደስ ያሰኘዋል ወይ? እያሉና እየመረመሩ መመላለስ ነው:: “ለጌታ ደስ የሚያሰኘውን እየመረመራችሁ እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ” ቁ. 10:: ይህ ለጌታ ያለንን ከፍ ያለ ፍቅር የሚያሳይ ነው:: ብዙ ጊዜ ኃጢአትን እንኳን እምቢ የምንለው ለራሳችን ስለማይበጀን፣ ጠላት በመንፈሳዊ ሕይወታችን እንዳይጎዳን ወዘተ በመፍራት ነው:: እነዚህ ሁሉ ትክክል ቢሆኑም፣ ከሁሉ የበለጠው ግን “ይህ ነገር ጌታዬን ደስ አያሰኘውም” ወይም “ጌታዬን በዚህ ነገር ላሳዝን አልፈልግም” በሚል በፍቅር ልብ ሲደረግ ነው:: በኤፌ 4፣30 ላይ በምናደርገው ክፉ ነገር መንፈስ ቅዱስ እንደሚያዝን ተመልክተናል:: ስለዚህ ኑሮአችን ጌታን ሊያሳዝንም ሊያስደስትም ይችላል ማለት ነው:: ብዙ ጊዜ ግን፣ ይህንን ነገር በውሳኔዎቻችን ውስጥ አናስገባም:: ለራሳችን የሚስማማውን ከማየት በስተቀር:: ክርስትናን ከሃይማኖት የሚለየው ግን አንዱ ዋና ነገር ይሄው ከጌታ ጋር ያለ የወዳጅነትና የግል ግንኙነት ነው:: እዚህ ላይ ግን ልብ ማለት ያለብን ነገር፣ ጌታን ደስ የሚያሰኘውን ለመመርመር በአእምሮአችን ወይም በልባችን መንፈስ መታደስ ያስፈልገናል:: ይህም የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥንና መታደስን የሚያመለክት ነው:: አስተሳሰባችን እንደ እግዚአብሔር ቃል ሊሆን ይገባል:: አስተሳሰባችንና አመለካከታችን ሳይታደስና ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ሳይቀራረብ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውን ነገር የመመርመር አቅሙም አይኖረንም:: አስተሳሰባችን ከዚህ ዓለም አስተሳሰብ የማይለይ ከሆነ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውን መመርመር ጨርሶ አንችልም:: “የእግዚአብሔር ፈቃድ፣ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነውን ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ [በአእምሮአችሁ (አ.መ.ት)] መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ::” ሮሜ 12፣2:: · የጨለማን ሥራ እየገለጡ መኖር በብርሃን መመላለስ ሌላው የሚይዘው ነገር፣ የጨለማን ሥራ መግለጥ ነው:: “ፍሬም ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ ይልቁን ግለጡት እንጂ” ቁ. 11:: በዚህ ክፍል “ግለጡት” ተብሎ የተተረጎመውን ቃል የግሪክ ሌክሲከን to convict (አንድ ሰው ጥፋት እንደሠራ ሁኔታን ወይም ነገርን ተጠቅሞ ማሳመን), refute (አንድ ሰው የተሳሳተ ሃሳብ ወይም አስተያየት ወዘተ እንዳለው ማረጋገጥ), confute (አንድ ሰው መሳሳቱን ወይም አንድ ሃሳብ ውሸተኛ መሆኑን ማሳየት) ብሎ ይተረጉመዋል:: ባጠቃላይ አንድ ሰው መሳሳቱን በሥራም ይሁን በንግግር ማሳየትና ወደ መረዳት እንዲመጣ ማድረግ ማለት ነው:: እንደ ተሳሳተ እንዲያምን ማድረግ ማለት ነው:: ስለዚህ የሚናገረው ክፉ የሚሠራውን ሰው ስለማጋለጥ ሳይሆን፣ ከሚሠራው ሥራ ጋር ባለመተባበር እንዲሁም ሌሎች ሁኔታዎችን ተጠቅሞ ሰውዬው እንዲወቀስና ስህተቱን እንዲያምን ማድረግ ማለት ነው:: ይሄንን ለመረዳት ምናልባት በዮሐ 8፣1-12 ያለውን በዝሙት ምክንያት ተይዛ በድንጋይ ልትወገር የነበረችውን ሴት ታሪክ ማጥናቱ ይረዳን ይሆናል:: በዚያ ክፍል ጻፎችና ፈሪሳውያን ከተማከሩበትና ከክፉ ሥራቸው ጋር ጌታ ሳይተባበር ነገር ግን ራሳቸው ደግሞ በደለኞች እንደሆኑ፣ የሚያደርጉትም ሥራ መልካም እንዳልሆነ ባደረገውና በተናገረው ንግግር ሲወቅሳቸውና ሲያሳምናቸው እንመለከታለን:: ይህ እንግዲህ የእነርሱን ክፉ ሥራ ወደ ብርሃን አውጥቶ ገለጸው ማለት ነው:: ስለዚህም በዮሐ 8፣12 ላይ እርሱ የዓለም ብርሃን እንደሆነ ይናገራል:: እዚህ ላይ ግን ልብ ማለት ያለብን፣ ሰዎች እንዳጠፉና ሥራቸው ክፉ እንደሆነ ለመውቀስና ወደ መረዳት እንዲመጡ ለማድረግ በመጀመሪያ ደረጃ ከክፉ ሥራቸው ጋር አለመተባበር ወሳኝ ነው:: ለዚህ ነው ጳውሎስም ስለዚህ ጉዳይ ሲናገር አለመተባበርንና መግለጥን አያይዞ የሚናገረው “ፍሬም ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ ይልቁን ግለጡት እንጂ” ቁ. 11:: ምክንያቱም አብሮ በክፉ ሥራ እየተባበሩ፣ ክፉ ሥራን መግለጥ የሚባል ነገር ስለማይሠራ ነው:: ማሳሰቢይ:- በቁ. 14 ላይ ያለውን ጥቅስ ጳውሎስ ከየት እንደጠቀሰው ሙሉ በሙሉ በእርግጠኝነት ባይታወቅም ምናልባት ኢሳ 26፣19ንና ኢሳ 60፣1ን አጣምሮ ሳይሆን አይቀርም የሚል ግምት አለ:: ሃሳቡ ግን የጌታን ብርሃንነትና በብርሃን ለመመላለስም የጌታ እርዳታ እንዳለ የሚያሳይ ነው:: 2)በጥበብ መመላለስ ቁ. 15-20 ጳውሎስ እንደ ብርሃን ልጆች ከሚመክርበት ምክሩ ጋር አብሮ የሚመክረው እንደ ጥበበኞች እንድንመላለስ ነው:: በዚህ ክፍል የጥበበኞችና ጥበብ የሌላቸው ወይም ሞኞች ልዩነት በግልጽ ተቀምጦአል:: በዚህ ክፍል ስለ ጥበበኞች የሚከተሉት ባሕርያት ተዘርዝረዋል:- · አኗኗራቸውን በጥንቃቄና በማስተዋል የሚመሩ “እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ” ቁ.15:: ይህም በዚህች በምድር ሕይወታቸው የሚያደርጉትን የሚያውቁና አካሄዳቸውና ኑሮአቸው በጥንቃቄ የሆነ ማለት ነው:: · ጊዜአቸውንና ሰዓታቸውን በማይሆን ነገር ሳይጠፉ፣ ለጌታ ነገር የሚያውሉ “ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ” ቁ. 16:: ይሄ “ቀኖቹ ክፍዎች ናቸውና” የሚለው አባባል፣ የዘመኑን ትውልድ፣ ሰው፣ አሠራር፣ ሥርዓት ወዘተ ክፋት የሚያመለክት እንጂ የሚነጋውንና የሚመሸውን ቀን ለማሳየት አይደለም:: ዘመኑ ሰዎች መልካም ሠርተውና እግዚአብሔርን ደስ አሰኝተው እንዲኖሩ የሚገፋፋ ዘመን አይደለም:: ሕብረተሰቡም ሆነ አሠራሩ (system) ሁሉ ለክፋት የሚገፋፋ ነው ለማለት ነው ማቴ 16፣4 የሐዋ 2፣40:: በይበልጥ ይሄንን ሃሳብ ለመረዳት ጳውሎስ በ2ጢሞ 3፣1-9 ላይ ስለ መጨረሻው ቀን የጻፈውን ማየቱ ይረዳል:: በዚያ ክፍል የመጨረሻውን ቀን “የሚያስጨንቅ ዘመን” ብሎ ይጠራዋል:: ከዚያ ወረድ ብለን ስናነብብ ግን፣ ቀኖቹ “የሚያስጨንቁ” የተባሉበት፣ የሰዎች ክፋትና ከእግዚአብሔር እየራቁና እያመጹ መሄድ እንጂ ስለ መንጋትና መጨለም እንደማያወራ እንረዳለን:: እንግዲህ ቀኖቹ ክፉዎች ስለሆኑና የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርገን እንድናልፍ በራሳቸው ስለማይገፋፉን፣ ጠበበኞች የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ ከፍለው ቀኖቹን መልካምና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ነገር ማድረጊያ ጊዜ ያደርጓቸዋል፣ ለመልካም ነገር ያውሎአቸዋል እንጂ እንደ ሞኞች በዋዛ በፈዛዛ ዘመናቸው እንዲያልፍ አያደርጉም:: በዚህ ክፍል “ዘመኑን ዋጁ” በሚለው አባባል፣ መዋጀት የሚለው ቃል መቤዠት ከሚለው ቃል ጋር ተመሳሳይ ትርጉም ነው ያለው:: ይሄውም የሚከፈለውን ዋጋ ከፍሎ ለራስ ማድረግ ማለት ነው:: መቤዠት የሚለውን የቃሉን ትርጉም በይበልጥ ለመረዳት ጥናት 2 ቁጥር 5ን ይመልከቱ:: · የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ የሚያስተውሉ “ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ::” ቁ. 17:: · ከወይን ይልቅ በመንፈስ ቅዱስ ዘወትር የሚሞሉ “መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ፣ ይህ ማባከን ነውና” ቁ. 18:: መንፈስ ቅዱስ መሞላትንና በወይን ጠጅ መስከርን ጳውሎስ ለምን እንዳወዳደረው ራሱ በዚህ ክፍል ባይገልጽም፣ አንድ ግን የተረጋገጠ ተመሳሳይነት አላቸው:: ይሄውም ወይን ጠጅ ወይም መጠጥ የሰውን ሥጋዊ ባሕርይና ጠባይ የሚገፋፋና ሥጋዊ ሥራዎችን (ለምሳሌ ስድብ፣ ጠብ፣ ዝሙት ወዘተ) እንዲያደርግ የሚያነሳሳ እንደሆነ ሁሉ፣ መንፈስ ቅዱስም መንፈሳዊውንና መልካሙን ነገር ሰው እንዲያደርግ የሚያነሳሳ፣ የሚያነቃቃና የሚያበረታታ ነው:: በዚህ ክፍል በወይን ጠጅ መስከር የሚያስገኘውን ውጤት ጳውሎስ ሲናገር በጥቅሉ “ማባከን” ይለዋል:: ማለትም የሚረባና የሚጠቅም ነገር አለማግኘትን፣ ብልሹነትንና ከመልካም ነገር መጉደልን የሚያመለክት ቃል ነው:: በአንጻሩ በመንፈስ ቅዱስ መሞላት የሚያስከትለውን ውጤት ስንመለከት የልብ ደስታ፣ ዝማሬና ምስጋና በዚህ ክፍል ተጠቅሰው እናገኛለን:: “በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ...” ቁ. 19:: ይህ ስለ ኳየሮች አገልግሎት የሚያወራ ሳይሆን፣ በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉ ሰዎች መንፈስ እንደሚሰጣቸው፣ ግጥም ሳያጠኑና ሳይዘጋጁ እርስ በርስ በመዝሙር መተናነጽን የሚያሳይ ነው:: ይህ አይነቱ በቅኔ መተናነጽ በዚህ ዘመን ጨርሶ ያልተለመደ ነገር ነው:: ምናልባትም ልንረዳውም ይከብደን ይሆናል:: ነገር ግን ሁል ጊዜ በመንፈስ ለሚሞሉ ሰዎች ይሄ አዲስ አይደለም:: በመንፈስ መሞላት እርስ በርስ በዝማሬ እንድንተናነጽ ብቻ የሚያደርግ ሳይሆን፣ ለጌታም በልባችን እንድንቀኝ ያደርጋል “...ለጌታ በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ” ቁ. 19:: ይሄም ስላጠናናቸውና ስለምናውቃቸው መዝሙሮች ብቻ ሳይሆን የሚናገረው፣ መንፈስ ቅዱስ በልባችን ስለሚሰጠንና ስለሚያስቀምጠው ዝማሬዎች ነው:: ከዚሁ ጋር ተያይዞም በመንፈስ ቅዱስ መሞላት የሚያስገኘው ውጤት የምስጋና ሕይወት ነው “ሁልጊዜ ስለ ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምላካችንንና አባታችንን ስለ ሁሉ አመስግኑ::” ቁ. 20:: ይህ በትዕዛዝና በህግ የሚገኝ ሳይሆን፣ በመንፈስ ቅዱስ ዘወትር የመሞላት ውጤት ነው:: ስለዚህ ጥበበኞች በወይን ጠጅ እየሰከሩ ብኩን ሕይወት የሚኖሩ ሳይሆኑ፣ በመንፈስ እየተሞሉ ግን ወንድሞቻቸውን የሚያንጹና ከጌታም ጋር በምስጋና ልብ የሚመላለሱ ናቸው:: · መንፈስ ቅዱስና አማኝ:- መጽሐፍ ቅዱስ በዋናነት በሶስት አይነት መልኩ የአማኝንና የመንፈስ ቅዱስን ግንኙነት ይገልጻል:: የመጀመሪያው አማኝ ወደ መዳን እንዲደርስና ከመንፈስ እንዲወለድ የሚያደርገው መንፈስ ቅዱስ በአማኝ ሕይወት የሚሠራው ሥራ ነው ዮሐ 3፣5-6 1ቆሮ 12፣3:: ያለ መንፈስ ቅዱስ ሥራ ድነት የሚባል ነገር የለምና:: ሁለተኛው መጽሐፍ ቅዱስ “መንፈስ ቅዱስን መጠመቅ” የሐዋ 1፣5 ወይም “መንፈስ ቅዱስን መቀበል” የሐዋ 8፣17 ወዘተ ብሎ የሚጠራውና በዘመኑም አነጋገር “መንፈስ ቅዱስን መሞላት” ብለን የምንጠራው ሲሆን፣ ይህም ከመጀመሪያው ልምምድ የተለየና አንድ አማኝ ካመነ በኋላ የሚያገኘው የአንድ ጊዜ የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ነው:: ይህ ሁለተኛው ልምምድ ከመጀመሪያው የተለየ መሆኑን በግልጽ ከሚያሳዩን ክፍሎች ውስጥ የሐዋ 8፣4-17 በቀደምትነት የሚጠቀስ ነው:: በዛ ክፍል ፊልጶስ በሰማሪያ ወንጌልን ከሰበከ በኋላ ብዙዎች እንዳመኑና በውሃም እንደ ተጠመቁ እናነብባለን “ነገር ግን ስለ እግዚአብሔር መንግሥትና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም እየሰበከላቸው ፊልጶስን ባመኑት ጊዜ፣ ወንዶችም ሴቶችም ተጠመቁ::” የሐዋ 8፣12:: ብዙዎች ወንጌልን ሰምተው አምነውና በውሃም የተጠመቁ ቢሆኑም፣ ገና ግን መንፈስ ቅዱስ እንዳልወረደባቸው ቀጥለን ስናነብብ እናገኛለን “በኢየሩሳሌምም የነበሩት ሐዋርያት የሰማርያ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ተቀበሉ ሰምተው ጴጥሮስንና ዮሐንስን ሰደዱላቸው:: እነርሱም በወረዱ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ይቀበሉ ዘንድ ጸለዩላቸው፣ በጌታ በኢየሱስ ስም ብቻ ተጠምቀው ነበር እንጂ ከእነርሱ በአንዱ ላይ ስንኳ ገና አልወረደም ነበርና:: በዚያን ጊዜ እጃቸውን ጫኑባቸው መንፈስ ቅዱስንም ተቀበሉ::” የሐዋ 8፣14-17:: ይህ እንግዲህ የሚያሳየን ስናምን የተለማመድነው ልምምድና በኋላ መንፈስ ቅዱስን መቀበል የሚባለው ደግሞ የተለያየ እንደሆነ ነው:: ባመኑ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው ቢሆን ኖሮ፣ እንደገና ጸሎት ባላስፈለገም ነበር:: ባመኑ ጊዜ ግን በአንዳቸውም ላይ መንፈስ ቅዱስ እንዳልወረደ ነው መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው:: ስለዚህም ነው የተለየ ጸሎት ያስፈለገው:: ብዙ ሰዎች፣ ሰው ካመነ በኋላ ለመንፈስ ቅዱስ ሙላት ሌላ ጸሎት እንደማያስፈልግና ባመንን ጊዜ ሁላችንም መንፈስ ቅዱስን እንደተቀበልን አድርገው ይናገራሉ:: መጽሐፍ ቅዱስ ግን ሁለቱ ልምምዶች የተለያዩ እንደሆኑ በግልጽ ያስረዳል:: ሶስተኛው አይነት አማኝ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያለው ግንኙነት፣ በዚህ በምናጠናው በኤፌ 5፣18 ላይ የተጠቀሰውና ዘወትር በመንፈስ ቅዱስ የመሞላትና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የቀረበና የማያቋርጥ ሕብረት ማድረግ ነው:: ይሄንን ለምሳሌ በየሐዋ 4፣31 ላይ በተለይ እንመለከታለን:: ምንም እንኳን በበዓለ ሃምሳ ቀን ደቀመዛሙርት በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉ ቢሆኑም፣ በጸሎት ከጌታ ጋር ሕብረት ሲያደርጉ ደግሞ በድጋሚ ሲሞሉ በዚህ ክፍል እናያለን:: መንፈስ ቅዱስ ለአንድ ለተወሰነ ወቅት ወይም ፕሮግራም ከእኛ ጋር የሚሆን ሳይሆን ለዘላለም ከእኛ ጋር ሕብረት እያደረገ በውስጣችን እንዲኖር የተሰጠን ነው:: አብ መንፈስ ቅዱስን ለፕሮግራም ሳይሆን ለእኛ ነውና የሰጠው ዮሐ 14፣15-17 2ቆሮ 13፣14::
Posted on: Thu, 25 Jul 2013 10:11:10 +0000

Trending Topics



Recently Viewed Topics




© 2015