የልጅነት እድሜ ጣሪያው ስንት ነው??? - TopicsExpress



          

የልጅነት እድሜ ጣሪያው ስንት ነው??? (Re-posted following graduation week) # Attention ድሮ ነው ልጅ እያለሁ (ድሮ ለካ እንዲህ ቅርብ ነው አሉ እቴጌ ጣይቱ፤ዲናህ ያዕቆብ በፌስ ቡክ ግድግዳዋ እንዳስነበበችኝ)፤የሁለተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ነው፤1987 ዓ.ም፡፡ አንዳንድ ጓደኞቼ የሶቅራጠስ ባች እያላችሁ ስታሽሟጥጡኝ ይሰማኛል፡፡ ግድ የለም ቦጭቁኝ፤አንዳንዶቻችሁ ዳይኖሰር ጋልባችሁ፤ከፊሎቻችሁ ደግሞ አብርሃም ድንኳን ሲተክል ካስማ ያቀበላችሁ ናችሁ!!! ሎል…ዕድሜ ጠጋ ነው፡፡ እዚች ላይ የወዳጄ ቢንያም ቤኖቪስኪ አበባው ዕድሜ ደጉ ግጥም ብትኖር እንዴት ጨዋታችንን ሸጋ ታደርገው ነበር፡፡ ወደ ዋናው ቁጭ ነገሬ ስገባ የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ አስተማሪዎቻችን ክፍል ውስጥ ልዩ ልዩ መዝሙሮችን ሲያስዘምሩ ቆዩና ማሳረጊያ መዝሙር ልጅነቴን ዘምሩ ተባለ፡፡ ሁሉም ተማሪዎች (አባቶቻችን ጭምር) ልጅነቴ ሲዘምሩ እኔ ቆፍጣናው እምቢዮ አልዘምርም ብዬ ፀጥ ረጭ አልኩ፡፡ አባቶቻችን ጭምር ያልኩት ክፍል ውስጥ ከነበሩ 25 ተማሪዎች ገሚሶቹ በአባቶቻችን ዕድሜ የሚገኙ በመሆናቸው ነው፡፡ ስሟን በትክክል የማላስታውሳት አስተማሪ ታዲያ እሳት ለብሳ እሳት ጎርሳ ለምንድን እንደማልዘምር ወደእኔ በመምጣት የማልዘምርበትን ምክንያት ስትጠይቅ የእኔ መልስ ልጅ መሆን አልፈልግም የሚል ሆነ፡፡ በምላሼ ይበልጥ የተናደደችው መምህርት የእኛ ጎረምሳ ከሚለው ኃይለ ቃሏ ጎን ለጎን 3 የቃሪያ ጥፊዎችን አልሳኝ ወደ ርዕሰ መምህሩ ቢሮ ወሰደችኝ፡፡ ጋሽ ማሙዬ ይባላሉ የያኔው ርዕሰ መምህር፡፡ በእድሜ ጠና ያሉና ተማሪዎችን እንደልጆቻቸው የሚመለከቱ ደግ ሰው ነበሩ፡፡ አሁን በህይወት የሉም ብለውኛል፡፡ (ነፍሳቸውን ይማር!!!) ጋሽ ማሙዬ…ፀጉሬን እንደእናት እያሻሹ በምን ምክንያት ልጅ መሆን እንዳልፈለግሁ ጠየቁኝ፡፡ (ልብ በሉ ያኔ ገና የስምንት ዓመት ጉብል ነበርሁ፡፡) እኔም የክፍል አለቃችን በእድሜው ትልቅ ስለሆነ እኛ ልጆች ስንጫወት እንደሚገርፈን፤ትልልቆች ለሽንት እንዲወጡ ፈቃድ ሲሰጣቸው እኛን እንደሚከለክለን (በዚህ ምክንያት አልፎ አልፎ ክፍል ውስጥ እንትን ሁሉ የሚያመልጣቸው ተማሪዎች ነበሩ)፤በስፖርት ክፍለ ጊዜ ኳስ ትልልቆቹ ሲጫወቱ በእድሜ የምናንስ ልጆች ኳስ ከማቀበል ያለፈ ዕድል እንደማይሰጠን፤በእርሻና እጅ ሥራ ትምህርቶች ለትልልቆቹ ተማሪዎች 99 ከመቶ ሲሰጥ (ያኔ መቶ ለተማሪ ስለማይሰጥ) በእድሜ ለምናንሰው ግን ከ50 ከመቶ በላይ ስለማይሰጠን (ምክንያት የእርሻና የእጅ ሥራ ትምህርቶች በአብዛኛው የጉልበት ሥራ የሚጠይቅ ስለሆነና በእድሜ የምናንስ ተማሪዎች አቅም ስለሚያጥረን)፤በሌላም በሌላም…ምክንያቶች ልጅ መሆን አልፈልግም!!! ይኸኔ ጋሽ ማሙዬ በአግራሞት ይመለከቱኝ ጀመሩ፡፡ በትምህርት ቤታችን በቂ ኳስ ስላልነበረ ለዚህ ቅሬታዬ መልስ ባላገኝም ለሌሎች ግን አስቸኳይ መፍትሔ ሰጡኝ፡፡ በልጅነቴ መዝሙር ፋንታ አባይ አባይ መዝሙር እንድዘምርም ተፈቀደልኝ፡፡ በሌሎች ትምህርቶች በማስመዘግበው ውጤት ልክም የእርሻና የእጅ ሥራ ትምህርቶች ውጤት እንደሚሞላልኝ ቃል ገቡልኝ፡፡ ያም ሆኖ ግን ልጅነቴን የሚያስወድድ ጉዳይ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ ዛሬም ድረስ የልጅ ነህ ተቀጥላ እየተከተለኝ…የትምህርት ዝግጁነቱ ሳያንሰኝ፣ነገሮችን የመከወን ድፍረቱና ኃለፊነት የተሞላበት የአሰራር ስልት ሳይጎድለኝ፤እውቀቱም ባይተርፈኝም ሳይጎልብኝ፤ ይኸን ኃላፊነት ለመወጣት ዕድሜህ ገና ነው (ያው በቅንፍ ልጅ ነህ መሆኑ ነው፤ምንም እንኳን ለቦታው የሚፈለገውን ሁሉንም መመዘኛዎች ከበቂ በላይ ባሟላም) እየተባልኩ ሕልሜን ከመኖር ስንቴ በዕድሜ አጥር ተከልያለሁ!!! የምር ልጅ አይደለሁም!!! የልጅነት እድሜ ጣሪያው ስንት ነው??? ወጣቶች የነገ አገር ተረካቢዎች ናቸው የምትል መፎክርም በፍጡም አትደላኝም፤ምክንያት ወጣቶች የዛሬ አገር ገንቢዎች ናቸውና!!! ሁሉንም የሥራና የኃላፊነት ቦታዎች በበርካታ ዓመታት የሥራ ልምድ ያካበቱ ሰዎች አስይዞ መጓዝ ጊያዜያዊ ጥቅምን ቢሰጥም እንደሀገር በረዥም ጊዜ የሚኖረው ጉዳ ግን የትየለሌ ነው፡፡ ይህን ጉዳይ በምሳሌ ለማስረዳት ያህል እንድን ወይፈን እርሻ ለማለማመድ ከአንድ ለረዥም ዓመታት ሲታረስ ከነበረ በሬ ጋር እንድ ላይ ጠምዶ ማረስ ሆነኛ አማራጭ ነው፡፡ ወይፈኑ ለበሬው ትኩስ ጉልበት ሲሰጥ በሬው ደግሞ ለወይፈኑ ልምዱን ያካፍላል፡፡ በዚህ ሂደት የዛሬው ወይፈን የነገ ሁነኛ የቀኝ ተጠማጅ ይሆናል!!! በዚህ ሁኔታ ወይፈኑን ለእርሻ ያላበቃ ገበሬ ነገ የሚጠምደው በሬ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ይኸ ሀቅ ግን በፊደል ባህር ሲዋኙ ለኖሩ ቀጣሪዎችና አሰሪዎች፤ለመንግስታችንም ጭምር የተገለጠ አይመስለኝም፡፡ እስኪ ለሥራ ቅጥር የሚወጡ ማስታወቂያዎችን ተመልከቱ፡፡ ከ98 በመቶ በላይ ሁለትና ከዚያ በላይ ዓመታትን የሥራ ልምድ የሚጠይቁ ናቸው፡፡ የበሰለ ምግብ ማን ይጠላል፤ጥሬውን አብስሎ መብላትም እኮ ታላቅነት ነው፡፡ ሁሉም የበሰሉ ምግቦች አንድ ወቅት ጥሬዎች ነበሩና!!! እውነት…ወጣቶችን ያገለለ የሀገር ልማት ልማት አይደለም!!! የሥራ ልምድ ስለሌላችሁ አንቀጥራችሁም፤ልጆች ናችሁ ማለትም ለሀገር ማሰብ አይደለም!!! በሀገራችን የሥራ አጥነት ችግር ላይ የተካሄዱ በርካታ ጥናቶችን ተመልክቻለሁ፡፡ በሀገራችን ያለው ወጣት ሥራ አጥነት መጠን እስከሀምሳ በመቶ ይደርሳል!!! ልብ በሉ በሀገራችን ካለው ጥቅል የሥራ አጥነት መጠን (37 በመቶ) አብላጫውን ድርሻ የሚወስዱት ወጣቶች ናቸው፡፡ ሁሌም ግን ወጣቶች የነገ ሀገር ተረካቢዎች ናቸው ይበላል፤እንዴት ለሚለው ግን መልስ የለም!!! እኔ በግሌ ፍርኃት ፍርኃት ይለኛል፤ወጣቶች ሥራ በማጣታቸው ወደሱሰኝነት፣ወጣት ጥፋተኝነት፣ወንጀለኛነትና መሰል ማሕበራዊ ቀውሶች ተጋላጭና ተጎጂ እየሆኑ ነው፡፡ በየዓመቱ ደግሞ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣት ምሩቃን ወደገበያው ይገባሉ፡፡ ሁሉም ቀጣሪዎች (መንግሥትን ጨምሮ) ወይ ልምድ ወይ የገዥ ፓርቲ የአባልነት ካርድ ይጠይቃሉ፡፡ ችግር እየተደራረበ፤የሥራ አጥነት መጠንም እየተቆለለ ሲሄድ ትምህርት የሚኖረው ጠቀሜታና የተሰጠው የማህበራዊ ዕሴት ሚዛን ክብደት እንደገለባ እየቀለለ ይሄዳል፡፡ ሩቅ በማይባል ጊዜም ማሕበራዊ ድንቁርና ይንሰራፋል፤ማሕበራዊ ድንቁረና የሚወልደው ተስፋ ቢስነትና የማንነት መንሸራተት እኛም ለሀገራችን ሀገራችንም ለእኛ ሳትሆን ለብልጣብልጥ ምዕራባውያን መፈንጫና መጫዎቻ አሻንጉሊት መሆናችን አይቀሬ ነው፡፡ ሳይደርቅ በእርጥቡ ሳይርቅ በቅርቡ እንዲሉ አበውና እመው ዛሬም አልረፈደምና ህብረተሰቡ፣የግልና ግበረሰናይ ደርጅቶች በተለይም መንግሥት ጉዳዩን የህልውና ጉዳይ አድርጎ ይመለከተው ዘንድ፤አፋጣኝ የመፍትሔ እርምጃዎችን ይወስድም ዘንድ እኔ እንደግለሰብ አሳስባለሁ፡፡ ዛሬ ለነገ እጽፋለሁ!!!
Posted on: Sun, 07 Jul 2013 12:04:12 +0000

Trending Topics



Recently Viewed Topics




© 2015