ድምጻችንይሰማዎች ሆይ! እስክንድር - TopicsExpress



          

ድምጻችንይሰማዎች ሆይ! እስክንድር አድንቋችኋል #Ethiopia #DimtsachinYisema ድምጻችን ይሰማን ተመልከቱ! ይህ የእስክንድር ነጋ መልዕክት ነው፡፡ #EthioMuslims ከጓደኞቼ ጋር በጠየቅነው ወቅት እንድናስተላልፍ አደራ ብሎናል፡፡ ድምጻችን ይሰማዎች ሆይ! እስክንድር አድንቋችኋል፡፡ ከሁለትና ሶስቱ ውጭ ቢሮ ውስጥ ተቀምጠው የሚውሉት ከ70 በላይ ፓርቲዎች ጉዳያችን አይደለም ቢሉትም እስክንድር ግን ቃሊት ሆኖ እያንዳንዱን እንቅስቃሴያችሁን ይከታተላል፡፡ መልዕክቱንም እንዲህ አስተላልፏል፡፡ ‹‹ድምጻችን ይሰማ ብለው የተነሱት ወጣቶቻችን ለፖለቲካው እንቅስቃሴም ትልቅ ተምሳሌት ናቸው፡፡ ሌላው ማህበረሰብም ሊደግፋቸው ይገባል፡፡ ወጣቶቹ ኢትዮጵያ ውስጥም አምባገነንን ሊያስጨንቅ የሚችል ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንደሚቻል በቀላሉ አስመስክረዋል፡፡ መብቱን በቀላሉ አሳልፎ የማሰጥ ወጣት እንዳለው አሳይተዋል፡፡ እስኪ አስቡት ይህ የወጣት እንቅስቃሴ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ቢሆን ምን ታዕምር ሊፈጥር እንደሚችል? እውነቴን ነው የምላችሁ ፓርቲዎችን ጨምሮ በፖለቲካው ዘርፍ እንቀሳቀሳለሁ የሚል አካል ድምጻችን ይሰማን ሞዴል ማድረግ ይኖርበታል››፡፡ እስክንድር እውነት አለው፡፡ እኔ በበኩሌ የማይዋዥቅ እንቅስቃሴ ያየሁት ድምጻችን ይሰማን ነው፡፡ ለሌላኛው የፖለቲካ እንቅስቃሴም ቢሆን ቀላል የማይባል ድምቀት ሰጥቶታል፡፡ በፖለቲካው ዘርፍ ብቻ ያተኮረው እንቅስቃሴን በተለይ በፌስ ቡክ በቅርብ አመታት ጠንከር እያለ ቢሆንም አጀንዳ ቀረጻው፣ አደረጃጀቱና እንቅስቃሴው አዝጋሚ ነው፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ ሲኖር፣ ባለሰልጣናት ሲመረጡ፣ ሲሻሩ፣ ሙስና ተከሰተ፣ መሬት ተሸጠ ሲባል ዜና ማስተላለፍ፣ ወቅታዊ ጉዳይን ማስተላለፍ ላይ የተጠመደ ነው፡፡ በእርግጥ ይህም አንድ በጎ ጅምር ነው፡፡ ሆኖም ትኩስ ጉዳይ ካላገኘ እንደገና ይቀዘቅዛል፡፡ አንዱን አጀንዳ ጥሎ ሌላ ከማንሳት ያለፈ ዳር የማድረስ ችግር ይታይበታል፡፡ ቀደም ብሎ የያዘው ጉዳይ (እስራት፣ የዜጎች መፈናቀል፣ ሙስና……) ዳር ሳይደርስ ሌላ አዲስ ወሬ ከመጣ ዋና አስመስሎት የነበረውን አጀንዳ በትኖ አዲሱን ይቀበላል፡፡ ያው ዋና አጀንዳው አልነበረውም ማለት ነው፡፡ አሊያም አጀንዳ ለመያዝ አቅም አልነበረውም፡፡ በዚህ ረገድ ድምጻችን ይሰማ የተለየ ነው፡፡ ኳስም ይኑር ሩጫ፣ ሙስናም ይሁር ሹምሽር በድምጻችን ይሰማ ሰፈር የሙስሊሙ ጉዳይ፣ የኮሚቴዎቼ ዜና አይደበዝዝም፡፡ በፖለቲካው ጉዳይ ግን በወረት አጀንዳዎች ዳር ሳይደርሱ ሌላኛውን ማንሳት የተለመደ ነው፡፡ አዲስ ዜና ያጠቃናል፡፡ በአሁኑ ወቅት ለጭቆና ራሱን መስዕዋት ያደረገውን የኔሰው ገብሬን እያስታወስነው አይደለም፡፡ ውብሸት ታዬን እኛ እረስተነው ያስተወሱት ፈረንጆቹ ናቸው፡፡ ከክልል የሚባረሩት ኢትዮጵያውያን የአንድ ሰሞን ጉዳይ ነው፡፡ ታሰረ፣ ተፈታ፣ ተገደለ፣ ሙስና…….ዜና ሆነው ያልፋሉ፡፡ ከሳምንት በኋላ በሳውዲ የሚሰቃዩትን ዜጎቻችንን ጉዳይ ረስተን ሌላ ጉዳይ እናነሳለን፡፡ ከዋናው ጉዳያችን ልቅ የኢህአዴግ ካድሬዎች የሚያነሷቸው ማስቀየሻዎች ላይ በርካታ ጊዜያችን እንገድላለን፡፡ እንደገና ሌላ ዜና ይመጣል፡፡ እኔ እንደሚመስለኝ ዋናው ችግራችን የተበታተንን በመሆናችን ነው፡፡ ፌስ ቡኩንም ሆነ ሌላውን እንቅስቃሴ በተደራጀ መለኩ፣ በሙያ፣ በስነ ምግባር የሚመራው አልተገኘም፡፡ ዲያስፖራውና አንዳንድ ፓርቲዎች አካባቢ የሚገኙ በጣት የሚቆጠሩ ግለሰቦች (በግል) ብቻ እንቅስቃሴ የትም ሊያደርሰው አይችልም፡፡ ማህበራዊ ድህረ ገጹ፣ ፖለቲካ እንቅስቃሴው የመሪ ያለህ እያለ ነው፡፡ በ1960ና 70ዎቹ ትውልድ በብጫቂ ወረቀት፣ በመልዕክተኛ፣ አልፎ አልፎም በቤት ስልክ ተገናኝተው ለራሳቸው ሳይሆን ለሰፊው ህዝብ ታግለዋል፡፡ በዛን ወቅት ፌስ ቡክ ቢኖር በየ ካፌና ጠባብ ቤቶች ተሰብስቦ የራሱን አገራዊ ፖሊሲ መቅረጽ የቻለው ያ ትውልዱ ምን ያህል ሊጠቀምበት ይችል እንደነበር መገመት አያዳግትም፡፡ ይህ ግን የአሁኑ ትውልድ በአጠቃላይ ችግር እንዳለበት የሚያሳይ አይደለም፡፡ ጥቂቶችም ቢሆኑ የአሁኑ ትውልድ በሙሉ የባከነ እንዳልሆነ እያሳዩን ነው፡፡ ድምጻችን ይሰማን በዚህ በፈዘዝነው መካከል ሆኖ መደራጀት፣ መጠየቅ፣ አጀንዳና ማንሳትና ዳር ማድረስ፣ አምባገነንን ማስጨነቅ ችሏል፡፡ ስለሆነም ድምጻችን ይሰማን መመልከቱ አዋጭ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ድምጻችን ይሰማ ሆይ! የኢትዮጵያውያን ድምጽ ጮህ ብሎ ይሰማ ዘንድ እናንተም አርዕያነታችሁን ተወጡ፡፡ የድሮው ትውልድ ፍልስጤም ድረስ ተጉዞ ሰልጥኗል፡፡ የሌሎች አገር ዜጎች እንኳን ስል አብዮት ብለው ኢትዮጵያ ድረስ መጥተው አሰልጥነዋል፡፡ አሁን ፌስ ቡክ የሚባል አውላላ ሜዳ ትልቅ ማሰልጠኛ ጣቢያ ሆኗል፡፡ እናም የዳሌ ምስል እየተከተለ ‹‹like›› የሚያደርገውን ወጣት፣ አንዱን ዜና ይዞ ሌላኛውን የሚያነሳውን፣ በአገር ጉዳይ አያገባኝም ብሎ ራሱን የሚሸነግለውን ስለ ትግል ስልት፣ ስል መደራጀት፣ ስለ አጀንዳ ቀረጻ ስልጠና ብትሰጡት፣ ‹‹ዱብ ዱብ›› እንዲል ብታደርጉት ምን ይመስላችኋል? — with Getachew Shiferaw.
Posted on: Mon, 11 Nov 2013 06:49:45 +0000

Trending Topics



Recently Viewed Topics




© 2015