ድምፃችን ይሰማ ‹‹ሕዝበ ሙስሊሙ - TopicsExpress



          

ድምፃችን ይሰማ ‹‹ሕዝበ ሙስሊሙ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ለተፈጠረው ብዥታ በይፋ ማብራሪያና ማስተባበያ እንዲሰጡ ይጠይቃል!›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ቃለመጠይቅ የፈጠረውን ብዥታ አስመልክቶ የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ ማክሰኞ ነሃሴ 6/2006 ከጥቂት ቀናት በፊት የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ከአንድ የዳያስፖራ ሬዲዮ ጣቢያ ጋር አንድ ቃለ መጠይቅ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ በዚህ ቃለ መጠይቅ ላይም ከኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጋር በተያያዘ አንዳንድ ነጥቦችን አንስተዋል፡፡ ዶክተሩ ዳያስፖራው መንግስት ያለአግባብ ሰዎችን እያሰረ መሆኑን በመቃወም የሚያነሳውን ወቀሳ አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱም በተድበሰበሰና ግልጽ ባልሆነ መልኩ ስለሙስሊም ታሳሪዎች በማውሳት የሚከተለውን አወዛጋቢ መልስ መስጠታቸውን ከታች የተያያዘው የቃለ መጠይቁ የድምጽ ቅጂ ያሳያል፡- ‹‹... ከዚህ በፊት በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ ጂሀድ ለመቀስቀስ የተቋቋሙ ሴሎች ነበሩ አገራችን ውስጥ፡፡ እነዚህ ሴሎች ከአገራችን ውጭ ሶማሊያም ሌላም ቦታ ስልጠና የወሰዱ ናቸው፡፡ እንግዲህ እነዚህ ሴሎች ታወቁ፡፡ የእኛ ሴኪውሪቲ እንደሚታወቀው ጠንካራ ነው፡፡ ክትትልም ያደርጋል፡፡ ገና ብዙ ችግር ሳይፈጥሩ ተያዙ፡፡ ከተያዙ በኋላ የበለጸጉ ሃገሮች ወዲያው ‹እንደዚህ ታስራላችሁ ሙስሊሞችን› የሚል አነሱ፡፡ ‹አይ እነዚህ ሰዎች በሃይማኖት አልታሰሩም፡፡ ግን የጂሀድ እንቅስቃሴ ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ ተይዘዋል፡፡ ሴሎችም መስርተው እንቅስቃሴ ጀምረው ነበር› ተብሎ ለማስረዳት ተሞከረ፡፡ ግን ብዙም አልተዋጠላቸውም፡፡ ከዚያ በኋላ ግን እነዚሁ በለጸጉ አገሮች ራሳቸው በተለይ አሜሪካንም ጨምሮ መጀመሪያ የታሰሩት ሰዎች ከዚሁ ሴል መስርተው የጂሀድ እንቅስቃሴ ለማድረግ እየሞከሩ እንደሆኑ ታውቆ የታሰሩት ሰዎች ጓንታናሞ ከታሰሩ ሌሎች አሸባሪዎች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው አወቁ፡፡ ይሄን ሲያውቁ መጥተው ‹እነዚህን ሰዎች እኛ ማነጋገር እንፈልጋለን፡፡ ልንጠይቃቸው እንፈልጋለን፡፡ እንዲህ አይነት ኮኔክሽን አግኝተናል፡፡ ስለዚህ ፍቀዱልን› ብለው ነው የመጡት፡፡ በግልጽ መነጋገሩ ጥሩ ነው ከሚል ነው... ›› ሚኒስትሩ ከላይ በተጠቀሰው ንግግራቸው ሁኔታውን ሲገልጹ ‹‹ከዚህ በፊት›› ሲሉ መግለጻቸው ጉዳዩ ኮሚቴዎቻችን ከመታሰራቸው በፊት ስለሆኑ ነገሮች የሚመለከት መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን ሚኒስትሩም በግል የትዊተር አካውንታቸው የተናገሩት ንግግር ኮሚቴዎቻችንን የሚመለከት አለመሆኑን የሚገልጽ ማስተባበያ ሰጥተዋል፡፡ ከጓንታናሞ ጋር በተያያዘ የተነሳው ነጥብም ንግግራቸው ከኮሚቴዎቻችን ጋር በፍጹም ሊገናኝ የማይችል ገለጻ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡ የአሜሪካ መንግስት አለማቀፍ የሃይማኖት ነጻነት ኮሚሽን አባላት እዚሁ አገራችን መጥተው በርካታ ሙስሊሞችን አናግረውና ነገሮችን አጣርተው ከሄዱ በኋላ የሚወክሉት መንግስታቸው እንኳንስ ኮሚቴዎቻችንን ከጓንታናሞ እስረኞች ጋር ማገናኘት ይቅርና የህዝበ ሙስሊሙን ሰላማዊ ጥያቄ አረጋግጠው ኮሚቴዎች እንዲፈቱ ከመጠየቅ ውጭ ያደረጉት ነገር የለም፡፡ እንግዲህ ይህ ሚኒስትሩ ያነሱት የጓንታናሞ ግንኙነት ጉዳይ ኮሚቴዎቻችንን በግልጽ የማይመለከት መሆኑን የሚያሳይ ነጥብ ቢሆንም እየመለሱት ያለው ጥያቄ በዳያስፖራው እንዲፈቱ ጥረት እየተደረገላቸው የሚገኙ ታሳሪዎችን የሚመለከት በመሆኑ እና ዳያስፖራውም እስካሁን በነበረው ሂደት እንዲፈቱ ጥረት ሲያደርግ የነበረው ብርቅዬ ኮሚቴዎቻችንን እና አጋሮቻቸውን አስመልክቶ የነበረ በመሆኑ ብዥታ መፍጠሩ አይቀርም፤ ፈጥሯልም፡፡ ይህ የሆነው ስለኮሚቴዎች እያወሱ በሚመስል ሁኔታ በአሸባሪነት ስለተፈረጁ ሰዎች በማንሳት የማቀላቀል ገለጻን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በመጠቀማቸው ነው፡፡ እስከዛሬ በነበረው ሂደት መንግስት የህዝበ ሙስሊሙን ሰላማዊ የመብት እንቅስቃሴ ለማጠልሸት እና ‹‹አሸባሪ›› ተብለው ከተፈረጁ ድርጅቶች ጋር ለማገናኘት ሲባዝን የቆየ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ካሁን ቀደም ‹‹ጂሀዳዊ ሀረካት›› በሚል ርእስ በኢቲቪ በቀረበውና ከኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ውግዘት ገጥሞት መሳለቂያ በሆነው ዘጋቢ ፊልም ላይ ይህን መሰል ያልተሳካ የማነካካት ሙከራ ተደርጓል፡፡ ‹‹ለሽብር ተግባር ሶማሊያ የሰለጠኑ የአልሸባብ አባላትና ሴሎች ናቸው›› በሚልም የተለያዩ ግለሰቦችን በዘጋቢ ፊልሙ ቢያካትቱም ከወኪሎቻችን ጋር ግን የሚያገናኙበት አንዳችም ስንጣሪ መረጃ በማጣታቸው ‹‹የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ›› ሲሉ በመግለጽ ብቻ ተቆጥበው አልፈውታል፡፡ ዛሬ ላይ ደግሞ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ምንም እንኳን ገለጻቸው ‹‹ከአልሸባብ ጋር በተያያዘ ይዘናቸዋል›› ባሏቸው ሙስሊም ታሳሪዎች ዙሪያ ያተኮረ ቢመስልም ይኸው የሙስሊሙን የመብት እንቅስቃሴ ከሽብርተኝነት ጋር ለማቀላቀል ዳር ዳር የማለት አባዜ ባንጸባረቀ መልኩ ቃለ መጠይቅ ሊሰጡ ሞክረዋል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ይህንን አደገኛ የማቀላቀል አካሄድ እንደህዝብ አጥብቀን እንቃወማለን፡፡ እንቅስቃሴያችን ህገ መንግስታዊ ሃይማኖታዊ መብቶቻችንን የማስከበር ዓላማ ብቻ ያዘለ መሆኑን ላለፉት ሶስት ዓመታት ያደረግነው በጽናት የታጀበ ሰላማዊ ትግል ይመሰክራል፡፡ ህዝብ ድምጹን ያሰሙለት ዘንድ የወከላቸው ብርቅዬ ኮሚቴዎቻችን ንጽህናም ህዝባዊ እውቅና ያለው እውነታ ነው፡፡ ይህንን እውነታም ሚሊዮኖች የፍትህ ጥሪያቸው አካል በማድረግ ደማቸውን አፍሰውለታል! አጥንታቸውን አሰብረውለታል! የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ራሱ በሚመርጣቸው ሰዎች የሚተዳደረው የአሜሪካ መንግስት ዓለም አቀፍ የሃይማኖታዊ ነጻነት ኮሚሽን (USCIRF) በኖቬምበር 8/2012 እና በጁላይ 22/2013 ባወጣቸው መግለጫዎች መንግስት በህዝበ ሙስሊሙ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ እየወሰደ ያለው የሃይል እርምጃ እና የመብት ጥሰት እንደሚያሳስበው እና በእስር ላይ የሚገኙት 29 ሙስሊም ጀግኖቻችንንም መንግስት በአስቸኳይ በነጻ እንዲለቅ መጠየቁ ይታወሳል፡፡ የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት Bureau of Democracy, Human Rights and Labor ያዘጋጀው የ2013 ዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብት አያያዝ ሪፖርትም ኢትዮጵያን አስመልክቶ ባዘጋጀው Country Reports on Human Rights Practices for 2013/Ethiopia ሪፖርት የህዝበ ሙስሊሙን ሰላማዊ ጥያቄ ለማስቆም መንግስት ሲወስድ የቆውን እርምጃ ደጋግሞ ጠቅሷል፡፡ እነዚህ መግለጫዎች የአሜሪካ መንግስት በብርቅዬ ኮሚቴዎቻችን እና ታሳሪዎቻችን ላይ ያለውን አቋም በግልጽ የሚያንጸባርቁ ናቸው፡፡ (የመግለጫዎቹ ሊንኮች ከታች ተያይዘዋል) ሌሎች በርካታ ዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማትም ታሳሪዎቻችን እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡ በመሆኑም እኒህና ሌሎችም በርካታ ሊስተባበሉ የማይችሉ ማስረጃዎች ባሉበት የህዝበ ሙስሊሙን ሰላማዊ የመብት ማስከበር እንቅስቃሴ በግልጽም ሆነ በተድበሰበሰ መልኩ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በአሸባሪነት ከተፈረጁ ድርጅቶች ጋር ማነካካት ተገቢ አለመሆኑን በማሳሰብ ሚኒስትሩ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ለተፈጠረው ብዥታ ይፋ ማብራሪያ እና ማስተባበያ እንዲሰጡ ህዝበ ሙስሊሙ ይጠይቃል! የሚኒስትሩ ቃለመጠይቅ የድምጽ ቅጂ ሊንክ፡- goo.gl/sOECPQ የአሜሪካ መንግስት ዓለም አቀፍ የሃይማኖታዊ ነጻነት ኮሚሽን የኖቬምበር 8/2012 መግለጫ ሊንክ፡- uscirf.gov/news-room/press-releases/uscirf-statement-uscirf-deeply-concerned-emerging-religious-freedom የአሜሪካ መንግስት ዓለም አቀፍ የሃይማኖታዊ ነጻነት ኮሚሽን የጁላይ 22/2013 መግለጫ ሊንክ፡- uscirf.gov/news-room/press-releases/uscirf-calls-ethiopia-release-religious-freedom-advocates-trial የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ያዘጋጀው የ2013 ዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብት አያያዝ ሪፖርት ሊንክ፡- state.gov/j/drl/rls/hrrpt/humanrightsreport/index.htm?year=2013& dlid=220113#wrapper ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል! ድምፃችን ይሰማ! አላሁ አክበር! (በድምፃችን ይሰማ የሚወጡ ጽሁፎች እና መግለጫዎች መብዛታቸው ሳይሆን ተደራሽነታቸው እና ተፅእኖ መፍጠር መቻላቸው ነው ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው! እርሶዎም መረጃዎችን በሚፈለገው መልኩ መከታተል እና መልእክቱን ለሁሉም እንዲደርስ ማድረግ ይጠበቅብዎታል!)
Posted on: Tue, 12 Aug 2014 17:46:38 +0000

Trending Topics



..sometimes kong the truth can hurt..the chief is rite..i must
You see this is what inspires us to be absurd because why not?
Hollywood CELEBRITY NEWS UPDATE!!! - Jackie Chan DEAD: DEATH of
Dennis Kucinich is busy creating a better USA, and a better world
For Sale! Protect your sneakers from dirt and have an organized

Recently Viewed Topics




© 2015