I am Very Sad!I felt irritated! So bad so frustrating! no word to - TopicsExpress



          

I am Very Sad!I felt irritated! So bad so frustrating! no word to explain this stupid and arrogant behavior and act.የግም ድግስ የሆነ ትውልድ!! …….ቪዲዮውን ይመልከቱ be zememelak Endria ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ እዚህ ከስር ያያያዝኩት ቪዲዮ ነው፡፡ ቪዲዮው በአንድ የግል ትምህርት ቤት ውስጥ የተቀረጸ ነው፡፡ ለአንዱ ጓደኛዬ አሳየሁት፤ ሀይማኖተኛ ቢጤ ነው ትንሽ ሲተክዝ ቆየና “የግም ድግስ የሆነ ትውልድ” ብሎ ጥሎኝ ሄደ፡፡ ይህንን የምጽፈው “ፍየል ገዝተን ቆዳውን ከፍየሉ በላይ በሆነ ዋጋ ሽጠን አተረፍን” የሚሉትን አልያም ደግሞ “ክትፎዬን ስልቅጥ አድርጌ ሁለት ብርሌ ጠጅ እላዩ ላይ ጥዬበት ሁለት ብር ከሀምሳ ብቻ ከፍዬ እያገሳሁ ወጣሁ” የሚባልበትን ጊዜ እያጣቀስኩ አይደለም ….. እኔ በሬ ተገዝቶ ፍየል የሚመረቅበት አልያም ደግሞ እንግዳ ቤት ሲገባ አልጋ ተለቆ፣ እግሩ በሞቀ ውሀ ታጥቦ፣ ጠቦት ታርዶ በአፍ በአፉ የሚጎረስበት ትውልድ ናፋቂ አይደለሁም፡፡ እኔ በዛም አነሰ የአዲሱ ትውልድ ተቋዳሽ ነኝ….ስልጣኔ የጠጣሁ ባልሆንም ገረፍ ገረፍ ሊያደርገኝ ሞክሯል፡፡ እንደዘመኑ ልጆች አጠራር ግን ‘ጌጃ’ ወይንም ‘ጥሬ’ ሆኜ አይደለም ይህንን ጽሁፍ የምጽፈው፡፡ እኔ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለሁ ከትምህርት በተረፈን ጊዜ ከጓደኞቼ ጋር ክበባትን አቋቁመን የልባችንን መሻት እንወጣ ነበር….. የእኔና የጓደኞቼ ትውልድ ለዚህ ትውልድ ቅርብ ነው፤ ልዩነታችን ግን የትየለሌ ነው፡፡ የከፍተኛ ተቋም ተማሪ ከሆንኩ በኋላም ቢሆን ይኸው ነው ታሪኬ፡፡ የዩኒቨርስቲ ተማሪ ሆኜ ትርፍ ጊዜ ሲኖረኝ እድሜ ለጓደኞቼ የአንተነህ ይግዛው፣ የደምሰው…. እና እጸገነት ላቀው መጣጥፎች የገናዬ እሸቱ ስዕሎች ፤ የቃለአብ እና ሮባ ለዛ ያላቸው ራፖች የዳዊት ከበደ ትረካዎች እና የብርሀኑ ከድር ቀልዶች የዮሀንስ ሞላ፣ የአበባ……. ግጥሞች እና ሌሎችም የማላስታውሳቸው፡፡ እባካችሁ የምታስታውሷቸውን አስተያየት ሳጥን ውስጥ በማስቀመጥ ውለታቸውን ዘክሩልኝ፡፡ ይህን ቪዲዮ ስትመለከቱ ትውልዱ ተቀራራቢ ነው…..ጨዋታው ግን ሌላ ነው፡፡ ሌላኛውን ጓደኛዬን አሳየሁት፡፡ ተበሳጨ…ፊቱን ቀጨመ “መንግስት የለም?…ህግ የለም?” ብሎ የፈረደበት መንግስት ላይ ፊት ለፊቱ የቆመ ይመስል አጉረጠረጠበት፡፡ “መንግስት ብቻውን ምን ያድርግ ጭናቸው ስር ገብቶ አይቆነጥጣቸው፡፡ ተጣሞ ያደገን መንግስት ያቃናዋል ያለህ ማነው?” ብሌ ሌላኛው ካድሬ ቀመስ ጓደኛዬ ገሰጸው፡፡ ”ትምህርት ቤቱ ነው እንጂ በጠራራ ጸሀይ መሰል ድርጊት ሲከናወን እሰየው ብሎ ግቢውን ፈቅዶ መፈንጫ ያደረገው፡፡ እኔ እንዴት አምኜ ልጄን ትምህርት ቤት እልካለሁ?” ገና ጉች ጉች እያለች ያለችውን ሴት ልጁን በአይነ ህሊናው ራቆቷን ስትጨፍር አይቶ ሌላኛው ተብሰከሰከ:: “ምን አገባችሁ እናንተ ቆይ እነሱ ቂጣቸውን ጥለው ለጨፈሩት ወይንስ ግዴታ አለምዬ ሶራ መጨፈር አለባቸው? ለምን ከጊዜው ጋር አትራመዱም? አለም እየተጓዘች ነው……..” ለዚህኛው ትውልድ ከእኛ በመጠኑ ቀረብ የሚል ጓደኛችን፡፡ “እንዲህም ብሎ መራመድ የለም…..ለምን መራመጃዬ ተሰብሮ አለም ብቻዋን አትሮጥም፡፡ ደግሞ ለዚህ ለብ ለብ ትውልድ ነው የምትከራከረው? ‘ላሊበላ የት ነው ሲባል ቴሌቪዥን ውስጥ’ ለሚል ትውልድ…..መቼ መሰረታዊውን ማንነቱን አውቆ ነው ደግሞ ቂጡን ጥሎ ትምህርት ቤት ውስጥ የሚጨፍረው?” . . . ወዴት እየሄድን ነው ጃል…..ሰምተን ዝም አይተን እልፍ እያልን እኮ ከማናልፈው እና ከማንወጣው ማጥ ውስጥ እየገባን ነው፡፡ ዳንስ መኖር የለበትም እያልኩኝ አይደለም ግን ትምህርት ቤት ውስጥ………ገና ለገና ወላጅ ተምሮ ቁም ነገር ላይ ይደርስልኛል ብሎ ተማምኖበት ልጁን በሚልክበት ግቢ ውስጥ ትውልድ ሲዘበራረቅ፡፡ ትምህርት ቤቶች ቀለም ትምህርት መስጠት ብቻ ሳይሆን መሰል ድርጊቶችን መከልከል አለባቸው……ወላጅ ብሩን እስከከፈለ ድረስ ምን አገባኝ ብሎ ጆሮ ዳባ ልበስ ማለት መስታወት ቤት ውስጥ እየኖሩ ድንጋይ ወርዋሪ ሰካራምን እንደመናቅ ነው፡፡ እኔ የድሮ ትውልድ ናፋቂ አይደለሁም…. ግን መጪው ጊዜን ከዚህ በተሻለ የምመኝ፡፡ ይህ ትውልድ ወዴት እየሄደ ነው?….ጓደኛዬ እንዳለው “የግም ድግስ ትውልድ” እየሆነ ነው እንዴ?
Posted on: Mon, 22 Dec 2014 09:02:17 +0000

Trending Topics



Recently Viewed Topics




© 2015