ማወቅ ብቻ አያኖርምና ኑሮን ኑረው /አቤል - TopicsExpress



          

ማወቅ ብቻ አያኖርምና ኑሮን ኑረው /አቤል በሬቻ/ ምድራችን ማወቅ በሚፈልጉ እልፍ አላፍት ሰዎች ፤ በሚያውቁ ጥቂቶችና በማያወቁ ብዙዎች የተሞላች ናት፡፡እውቀት ትፈለጋለች፡፡ በአዋቂዎች አለም ላይ አላወቂ ሆኖ መገኘት የበደሎች ሁሉ በደል ፤የኪሳራዎች ሁሉ ኪሳራ ነው፡፡ ይህ ሁሉ እንዳለ ሆኖ እኔ የሚገርመኝ ምንም የማያውቁ ወይም ምንም ስለማወቅ ቁብ የማይሰጣቸው ጥቂት ሰዎች ከአዋቂዎች በተሻለ ደረጃና የኑሮ ከፍታ ላይ መኖራቸው ነው፡፡ እስኪ ደልቷቸው ስለ ሚኖሩ ልጥጥ ባለፀጎች ለትንሽ ግዜ አስቡ የማነሳው ሀሰብ ሁሉንም ባይመለከት እንኳን ግማሹን ይነካል ብዬ አስባለው፡፡ ህይወት ተገላቢጦሽ ናት፡፡ በመማር ብዛት ፀጉራቸውን ያሸበቱ ነገር ግን የሚኖሩበት የግል ቤት የሌላቸው በኪራይ ቤት እየተሰቃዩ የሚኖር ስንትና ስንት የዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎችን ፤ የኮሌጅ ዲኖች አውቃለሁ፡፡ኑሯቸው እዚህ ግባ የማይባል ፤ ጫማቸው የተሻፈፈ፤ ልብሳቸው የተቀደደ ፤ የባስ ትኬት እየቆረጡ አመቱን ሙሉ በሀምሳ ምናምን ቁጥር ባስ የሚሳፈሩ የሚያሳዝኑ ስታያቸው ‹‹መማርና ማወቅእንደነሱስ ……….ከሆነ ከማወቅ አለማወቅ ይሻላል›› የምትልላቸው ምስኪን ሰዎች አሉ ፡፡ ማንም ያላየውን በማየትና ስለ ህይወት በመናገር ብዙዎችን በጥበብ ስራቸው ያስደነቁ አዋቂዎች ነገር ግን የህይወት ቱባ ውሉ የጠፋባቸው የሰው እጅ እያዩ የሚኖሩ በርካታ የጥበብም ሰዎች አሉ፡፡ ስለነሱ ሳስብ የZewdalem Tadesse .ፅሑፍ ትውስ ይለኛል፡፡ ዘውድ አለም ስለ እነዚህ ሰዎች እንደዚህ ይላል ‹‹ በ70 ና በ80ዎቹ እንደነበሩት ጸሀፍት እንዳትጃጃል "ለጥበብ ዋጋ ልክፈል" ምናምን ብለህ እራስህን እንዳታቄል....ሀብታም ጸሀፊ ለመሆን ጣር እንጂ ፌስታል ለልጁ ሚያወርስ ችጋራም አትሁን ....ትናንት በወጣትነታቸው ሳይሰሩ ስነጽሁፍን ብቻ የሙጥኝ ብለው የኖሩትን ሰዎች ወደብሄራዊ ቲያትር አካባቢ ሄደህ ሹፋቸው.... ግማሾቹ ለቀዋል...ግማሾቹ ለፈራንካ ብለው ለማያምኑበት መንግስት እያሽቋለጡ ለአሰሱም ለገሰሱም በስብሰባ ብትል በፓናል ውይይት ግጥም እየጻፉ ሆዳቸውን ሲሞሉ ታገኛቸዋለህ....ጥቂቶቹ ደግሞ የሀብታም አጫዋች (የሳሎን ውሻ) ሆነው እየኖሩ ነው..... ›› የአስተሳሰብ ሀብታም ሆኖ የኑሮ ደሃ ፤ የአውቀት ባለፀጋ ሆኖ የገንዘብ ነዳይ መሆን አለ፡፡ ደሞ በዚህ ጥግ ያሉ የኑሮ ጭንቀት ያላጎበጣቸው ስለሚኖሩበት የተጣለለ ቤት የማያስቡ በአመት የሚያወጡት ወጪያቸው ሲታይ የነሱ ገንዘብ ብዙ ደሃ ሰዎችን መርዳትና ማኖር የሚችል ሆኖ ምናገኘው ፤ ስለሚለብሱት ልብስ ማርክ የማያውቁ ግን የሚለብሱት ልብስ በብዙ ሺዎች የሚሸምቱ ፤ የሚነዱትን መኪና ብራድ የማያውቁ ነገር ግን አዳዲስ ሞዴል መኪና ሊያውም ባለ እረዥሙን ሽንጣም መኪና የሚያሽከረክሩ በከተማችን ሞልተዋል፡፡ እነዚህ ፊደል ያልቆጠሩ ፀረ እውቀት የሆኑ ሰዎች ብዙ የተማረና እድሜውን አውቀትን ሲፈልግ ሲጠማ የኖረን ሰው ሰብስበው የሚያስተዳድሩ ፤ ከራሳቸው የህይወት መዘውር ውጪ ስለ ሚኖሩበት አለም ፍልስፍና ፤ የጥበብ ስራና ፖለቲካው ቁብ የማይሰጣቸው ነገር ግን ከተማረው በላይ ሰውን በተለይም ተተኪውን ትውልድ የሚማርኩና የሚያስቀኑ ፤ በአይምሯቸው ሳይሆን በገንዘባቸው ልክ የመያስቡ አይነት ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለት ወገኖች ሳስብ ታድያ ጥያቄ በአይምሮዬ ይመላለሳል ፡፡ ህይወት እንዲህ ከሆነ ታድያ የማወቅ ትርፉ ምንድነው ? ሰው ለምን አዋቂ መሆንን መባልና ይፈልጋል ? አወቂ ለማኝ መሆን ነው ወይስ አላወቂ ባለፀጋ መሆን ጉዳት ያለው ? ህይወትን ሚዛናዊ አድርጎ አዋቂም ባለፀጋም የሆነ ምሳሌ የሚሆን ሰው እናገኝ ይሆን ?
Posted on: Wed, 25 Sep 2013 06:29:42 +0000

Trending Topics



Recently Viewed Topics




© 2015