ውሸትና ጾም ጥያቄ፡- ከልጅነቱ ጀምሮ - TopicsExpress



          

ውሸትና ጾም ጥያቄ፡- ከልጅነቱ ጀምሮ ውሸት የለመደበት ሰው አለ እንበል። ነገር ግን ይህን ክፉ ልምድ ለማጥፋት እየታገለ ነው። ነገር ግን እየዘነጋ ይዋሻል። ከዚያም አላህን ምህረት ይለምናል። እና ይህ ሰው በውሸቱ ምክንያት ጾሙ ይበላሻል? መልስ፡- በአላህ ሥም እጅግ አዛኝ ሩህሩህ በሆነው። በቅድሚያ ሙስሊሞችን ሁሉ አላህ እንዲያነቃቸው፣ ደካማ ጎኖቻቸውን እየገመገሙ እንዲታረሙ እንዲረዳቸው አላህን እንለምናለን። አላህን ከሚያስቆጡ ነገሮችም እንዲርቁ እንዲያደርጋቸው እርሱኑ እንማጸናለን። መልሳችንን ውሸት እርም እና አስከፊ ኃጢያት መሆኑን በመናገር እንጀምር። ለእውነተኛ ምእመናን የማይገባ መጥፎ ባህሪም ነው። ውሸት የሙናፊቅነት መገለጫ ነው። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- “ሙናፊቅ ሦስት ባህሪያት አሉት። ውሸት ያወራል። ቃሉን ያፈርሳል። እምነት (አደራ) ይክዳል።” (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)። በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- إِنَّمَا يَفْتَرِي الْكَذِبَ الَّذِينَ لَا يُؤْمِنُونَ بِآيَاتِ اللَّهِ وَأُولَٰئِكَ هُمُ الْكَاذِبُونَ [١٦:١٠٥] “ውሸትን የሚቀጣጥፉት እነዚያ በአላህ አንቀጾች የማያምኑት ብቻ ናቸው፡፡ እነዚያም ውሸታሞቹ እነሱ ብቻ ናቸው፡፡” (አን-ነሕል 16፤ 105) ቡኻሪ ከሰይዲና አቡሁረይራ (ረ.ዐ) ይዘው እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- “ያ ውሸት መናገርና በርሱ መስራት የማይተው ሰው ምግቡንና መጠጡን መተዉ ለአላህ አይገደውም።” “ውሸት መናገር” የሚለው ሐረግ ቅጥፈትን፣ ሐሜትን፣ ነገር ማዋሰድን፣ የውሸት ምስክርነትንና ማንኛውም ሐራም የሆነን ንግግር ያካትታል። አል-ሐፊዝ ኢብኑ ሐጀር እንዲህ ይላሉ፡- “ምግቡንና መጠጡን መተዉ ለአላህ አይገደውም” የሚለውን ሐረግ አስመልክቶ ኢብኑ በጠል እንዲህ ብለዋል፡- ‘ይህ ንግግር ሰውየው ጾም መጾሙን መተው አለበት ማለት አይደለም። ይልቅ ጾመኛ የሆነ ሰው የተዘረዘሩትን ክፉ ንግግሮች መተው አለበት ለማለት ነው። ካልሆነ ግን ጾሙ ተቀባይነት እንደማይኖረው አስረጁ ክፉ ንግግር አለመተዉ ነው። ሐዲሱ በጥቅሉ እያስተላለፈ ያለው መልእክት በውሸት የተሞላ ጾም ተቀባይነት እንደሌለውና ከውሸት ያገለለ ጾም ደግሞ ተቀባይነት እንዳለው ነው።” ኢብኑል ዓረቢይ እንዲህ ይላል፡- “ይህ የተጠቀሰው ሐዲስ የተጠቀሱትን ክፉ ነገሮች የሚፈፅም ጾመኛ የጾም ምንዳ እንደማይከፈለው ይጠቁማል። ይህም ማለት በጾም የሚገኘው ምንዳ በውሸትና በተጠቀሱት ነገሮች ከሚኖረው የኃጢያት ሸክም ጋር አይመጣጠንም።…” ከላይ በተጠቀሱት ዑለሞች አንደበት እንደተጠቀሰው ጾም በተለያዩ ኃጢያቶች ይጠቃል። አንዳንዶቹ የጾምን ምንዳ ያቀጭጫሉ። ሌሎቹ ደግሞ ያወድሙታል። ስለዚህ ውሸት የለመደበት ሰው በራሱ ላይ መልፋትና መድከም ይገባዋል። ይህን መጥ ልምድ ለማሸነፍ ነፍሱን ማሸነፍ አለበት። ሁሌም ሲዋሽ ወደ አላህ መመለስና ተውበት ማድረግ አለበት። ከኃጢያቱ የሚመለስና ተውበት የሚያደርግ ሰው ልክ ኃጢያት እንደማይፈጽም ሰው ነው። አላህ የተሻለ ያውቃል! source: ethiomuslim https://facebook/pages/የረመዳን-24ሰዓት-ዳዕዋ/137858589745672?hc_location=timeline plz share የረመዳን 24ሰዓት ዳዕዋ የረመዳን 24ሰዓት ዳዕዋ
Posted on: Wed, 10 Jul 2013 14:51:16 +0000

Trending Topics



Recently Viewed Topics




© 2015