የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቃውሞን - TopicsExpress



          

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቃውሞን የምደግፍባቸው ሶስት ምክንያቶች የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ተቃውሞ ሀላፊነት የማይሰማው መንግስት ወደማይፈለግ አቅጣጫ እየገፋው ነው፡፡ ጉዳዮቹ ተገፍተው ሌላ መልክ ይዘው ወደ አስከፊ ሽብር ከማምራታችን በፊት ይህንን ቀውስ ለማስቀረት ሙስሊም ያልሆነን ኢትዮጵያውያን የድርሻችንን መወጣት ያለብን ይመስለኛል፡፡ የጠላቴ ጠላት በሚል ጠባብ ስሌት ሳይሆን መርህን መሰረት ያደረገ አስተዋጽኦ ማድረግ ይገባናል፡፡ ይህም ከጭፍን ድጋፍና ተቃውሞ ያወጣናል፡፡ በመንግስት ሚዲያዎች ተራ ፕሮፖጋንዳ ከመወሰድም ያድነናል፡፡ ከዚህ በሚመነጭ ቅን ልቦና ተቃውሞውን የምደግፍባቸውን ሶስት መሰረታዊ ምክንያቶች ለማስቀመጥ እሞክራለው፡፡ የመጀመሪያው ሙሉ ምስሉን ከማንበብ የሚቀዳ ነው፡፡ ከነጠላ ጉዳዮች ይልቅ አጠቃላይ ጉዳዮችን መረዳት ይቀናኛል፡፡ ከአንድ የታሪክ ክስተት ይልቅ የሰው ልጆችን ታሪክ ብማር እመርጣለው፡፡ በሆነ የታሪክ አጋጣሚ የተደረጉ ነገሮችን ቢማርኩኝም አጠቃላይ የሐሰሳዬ ማጠንጠኛ እንዲሆኑ አልፈቅድም፡፡ ያ ትውልድ የዚህችን ሀገር ተስፋ እንደቀበረ ከሚያስቡና ይህን የተቀበረ ተስፋ እዚያ ትውልድ ውስጥ ፈልጎ ከተቀበረበት ለማውጣት ከሚለፉትም ወገን አይደለሁም፡፡ ታሪካቸው የሚማርክ ነገር ስለማይጠፋውና አሁንም ከፖለቲካው ምህዳር ባለመጥፋታቸው (ገዢዎቻችንም እነርሱው ሰለሆኑ) በጉጉት እንደማነባቸው አልሸሽግም፡፡ ነገር ግን የአንዳንድ ክስተቶች ተጽእኖ ምንም ቢጎላ ከአጠቃላይ ምልከታው አይበልጥም የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከዚህ በመነሳት ነው፤ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቃውሞን ከግብጹ ‘ሙስሊም ብራዘርሑድ መር’ እንቅስቃሴ ለይቼ የማላየው፡፡ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ከሌላው ዓለም በተለየ በሀገሪቱ ካሉ የሌላ እምነት ተከታዮች ጋር አስማምቶ የሚያኖር ቀለም አላቸው፡፡ ይህ ቀለም በእምነቱ ልሂቃን ምን አይነት ትንታኔ እንደሚሰጠው ለመረዳት እጅግ የሚከብድ ይመስለኛል፡፡ ይህን የፈጠረው በእምነቱ ተከታዮች ላይ የደረሰ ታሪካዊ ጭቆና ይሁን የነብዩ መሐመድ ‘ኢትዮጵያን አትንኩ’ የሚል ትዕዛዝ፤ወይስ እምነቱ በሀገሪቱ የተስፋፋበት መንገድ ይሁን የእስልምና ሰላምን የሚሰበክ አስተምህሮ(doctrine) የሚለው በጥናት ቢደረስበት መልካም ነው፡፡ በተጨማሪም ጥናቱ ነገን እንዴት እንኑር የሚለውን ቢያካትት ደግሞ እጅግ ብዙ በጎ ትሩፋቶች ያበረክታል ብዬ ተስፋ አደርጋለው፡፡ ነገር ግን እስልምና ሀገር በቀል እምነት አይደለም፤ እንደ ክርስትና እና ይሑዲ ከመካከለኛው ምስራቅ ወደሀገራችን የዘለቀ ነው፡፡ ይህም በሌላ ሀገር ካሉ የእምነቱ ተከታዮች ጋር የሚጋራው ነገር ከሚለየው እንዲበልጥ ያደርጋል፡፡ ተመሳሳይ ነጽሮተ ዓለም(worldview) ያላቸው ሰዎች ከሌላቸው ይልቅ በብዙ ጉዳዮች እንደሚግባቡ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ አረንጓዴ መንጸር ያጠለቀ፣ ሁሉም ነገር አረንጓዴ፤ ቀይ መነጽር የለበሰው ደግሞ ሁሉም ነገር ቀይ እንደሚመስለው ማለት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት በግብጽ፣ በማሊ፣ በኢራቅና በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሙስሊሞች የአለማችንን አካሄድ ተመልክተው ተቀራራቢ የሆነ ምልከታ እና ንጠቀት (reaction) ቢኖራቸው የሚያስገርም አይደለም፡፡ የገረመው ካለ አንድ ቁራን እንደሚቀሩ፣ አንድ ሐፊዝ እንደሚያፍዙና አንድ ሐዲስ እንደሚያሄዱ ያልተረዳ ነው፡፡ እነዚህ ቅዱሳት መጽሐፍትና እስላማዊው ትውፊት ነጽሮተ ዓለማቸውን ያበጁታል፡፡ ይህንን መሰረት አድርጌ ነው የኢትዮጵያን ሙስሊሞች እንቅስቃሴ ከግብጽ ሙስሊሞች ጋር የማመሳስለው፡፡ ይህንን ስል ግን የኢትዮጵያ መንግስት እንደሚያደርገው ከዓለም አቀፍ ጽንፈኛ አሸባሪዎች የመቀላቀል ተራ ፍረጃ ጋር እንዳይመድበኝ አንባቢው ይጠንቀቅ፡፡ እንደሚታወቀው ሴኩላሪዝም የዓለማችንን እምነቶች መፈታተን ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ይህንን የተረዱ የተለያዩ እምነቶች የየግላቸውን እርምጃ እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡ ከሁሉም እምነቶች እንደ እስልምና በፈረጠመ ክንድ የተከላከለው የለም፤ በተለይ በመካከለኛው ምስራቅና ሰሜን አፍሪቃ ይህ ትንቅንቅ በጉልህ ይታያል፡፡ በግሎባላይዜሽን አማካኝነት አለም ወደ አንድ መንደር ተቀይራለች፤ ማንም ቢሆን ይህን ይቀር ዘንድ አይቻለውም፡፡ ነገር ግን አለም አንዲት መንደር ስትሆን ሀይማኖቷ ምን ይሆን የሚለው ብዙዎቹን የሞት የሽረት ትግል ውስጥ ከቷቸዋል፡፡ ሴኩላሪዝም በዴሞክራሲ ጀርባ አድብቷል፤ በግብጽ ይህን የተረዱ የሙስሊም ብራዘርሑድ ሰዎች እንደ ጠላታቸው ተደብቀው መንበረ መንገስቱን ጨበጡ፡፡ ነገር ግን ጨዋታውን እንደ ቅድመ ምርጫው ሊካኑበት አልቻሉም፡፡ የወሰዱዋቸው እርምጃዎች መሰረታዊ የዴሞክራሲ መርህን የሚጥስ በመሆኑ ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ መንገዶች ሁሉ ከመዘጋታቸው በፊት መላ እንበለው ያሉ ሰዎች አደባባይ ወጥተው በወታደሩ ድጋፍ የሙርሲን መንግስት ገለበጡት፡፡ አሁን ብዙም ያልተወደደው ብልጠት ሳይሆን የከፋው ጠብመንጃ ግብጽን እየገዛ ነው፡፡ የኢትዮጵያም ሆነ የግብጽ ሙስሊሞች ጥያቄ ተገቢ ነው ብዬ አምናለው፡፡ ሀይማኖትን ከሀገር መዋቅርና እንቅስቃሴ በሚያገል ስርዓት አላምንም፡፡ ከሙስሊም ብራዘርሁድ ጋር በተፈጠረው ችግር ላይ እስማማና ነገር ግን መፍትሄ ተደርጎ በተቀመጠው እስላማዊ መንግስት ልዩነት አለኝ፤ ይህም በሀገሪቱ የሚገኙ ሴኩላርና ሌሎች እምነቶችን ከግምት ያላስገባ በመሆኑ ነው፡፡ አለማችን የብዝሃ ነጽሮተ ዓለምን የሚቀበል አዲስ ስርዓት ያስፈልጋታል፡፡ይህ በዘመናችን የሰው ልጅ መመለስ ያለበት መሰረታዊ ጥያቄ ነው፡፡ ምዕራባውያኑ ለዚህ መልስ ያላቸው፣ በመጽሐፋቸውም የሰፈረ አይመስለኝም፡፡ ካለ ግን ጠቁሙኝ ላነባቸው ዝግጁ ነኝ ለጊዜው ግን አይኖቹ በጨርቅ ተሸፍኖ እንደሚንገላወድ ሰው ናቸው፡፡ ሴኩላሪዝም ጸረ እምነት ነው፤ የአንድ እምነት የበላይነት ደግሞ ሌሎች እምነቶችን ብቻ ሳይሆን ስለእምነት ግድ የማይሰጣቸውን የሚደፈጥጥ ነው፡፡እነዚህን ሁለት ተጻጻራሪ ሀሳቦች የሚያስታርቅ ነገር የግድ ያስፈልጋል፡፡ ወደ ሀገራችን ስንመጣ የኢህአዴግ መንግስት በሌሎች ጉዳዮች እንደሚምታታበት ሳይሆን ባልተለመደ መልኩ እምነቶች ላይ ጥርት ያለ አቋም እንዳለው አሳይቷል፤ ከደደቢት እስከ አራት ኪሎ አልዋዠቀም፡፡ እምነቶችንና ምእመናንን ከሀገሪቱ ጉዳዮች ከማግለሉ አልፎ ተርፎ በቀሚስ ለባሽ ካድሬዎች እንዲመሩ በማደረግ ወደፈለገው አቅጣጫ ሲያሾራቸው ቆይቷል፤ ይህም አንድ ዐሳብ ብቻ ይነገስ ከሚለው ዶግማው ጋር መሳ ለመሳ ይሄዳል፡፡ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ከበረሃ ጀምሮ ባሰረጋቸው የሐሰት መነኮሳትና በብሔር ፖለቲካ ዳግም ባጠመቃቸው የቤተ ክህነት ሰዎች እንዳሻው ይቆጣጠረዋል፡፡ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጉባኤ በመጀመሪያዎቹ አስር አመታት አንጻራዊ ነጻነት የነበረው ቢሆንም የኋላ የኋላ እንደሌሎቹ እምነቶች ከመሸበብ አልዳነም፡፡ በቅርቡ ለንባብ በበቃው መጽሐፋቸው ዶ/ር መረራ ጉዲና ይህንን ሁኔታ እንዲህ ሲሉ ይገልጹታል፡፡ “ . . .ከሀገራችን የሀይማኖት አባቶች ጋር እምነቴ ለመጨረሻ ጊዜ የተናጋው ምርጫ 97ን ተከትሎ በተፈጠረው ቀውስ ምክንያት ነው፡፡ ምርጫውን ተከትሎ ቀውሱ እየሰፋ ሲሄድ፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የሃይማኖት አባቶች አንድ ነገር እንዲያደርጉ እየሞከርኩ ስለሆነ አንድ እናነጋግራቸው ብሎ ጠራኝ . . . በጣም የተከፋሁት ግን ፓትርያርኩም ሆነ ሌሎች ሌሎች የእምነት አባቶች በሰጡት አስተያየት ነበር፡፡ ቤታቸው ስለሆነ ወይም በሃይማኖት አባቶች መካከል ሊኖር በሚችለው የፕሮቶኮል ልዩነት አላውቅም፣ ውይይቱን የጀመሩት ፓትርያርኩ ነበሩ፡፡ በውስጣቸው ንዴት እየተሰማቸው እግዚአብሔርንም፣ መንግሥትንም አታከብሩም ብለው ብዙ የግሳጼ ንግግር ዘበዘቡ፡፡ የሙስሊሙ ሼህም ከፓትርያርኩ ለመብለጥ በሚቃጣው ቋንቋ የፈሰሰው ደም በተቃዋሚዎች ምክንያት እንደሆነ ነገሩን፡፡ ትንሽም ቢሆን የሚያውቁኝ የመካነ ኢየሱስ ቄስ ኢተፋ ጎበናም እኛን ለመደገፍ ይቅርና እውነቱን ለመናገር አልደፈሩም፡፡ ከሁለቱም ወገኖች ሊያጠፉ ይችላሉ፤ ሁለቱም የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆኑ የኛ ፈንታ ሁለቱንም ማስታረቅና ደም እንዳይፈስ ማድረግ ነው ብለው ሚዛኑን ለመጠበቅ የሞከሩት የካቶሊኩ የሃይማኖት አባት ብቻ ነበሩ፡፡ . . .” በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያ ሙስለሞች የሚያደርጉትን ተቃውሞ እደግፋለው፡፡ ሁለተኛው የድጋፌ ምክንያት ትግሉ ነውጥ አልባ መሆኑ ነው ፡፡ ግብጽ አሁን አሁን የሰው ህይወት እንደቀልድ የሚቀጠፍባት ሀገር ሆነች እንጂ በሁለት ዓመታት ውስጥ አለምን ያስደመሙ ሁለት ነውጥ አልባ አብዮቶች አካሂዳ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችም ለበርካታ ወራት የዘለቀ፣ እጅግም ያልተለመደ ከነውጥ የራቀ ትግል ውስጥ አልፈዋል፡፡ ይህም አጠቃላይ ምልከታዬን ለማስረዳት ሳይጠቅመኝ አልቀረም፡፡ ስለ ሰላማዊ ትግል አንስተን ጋንዲን አለመጥራት ነውር ነው፡፡ በዚህ ክፍለ ዘመን ስማቸው ከሚነሳ ታላላቅ ሰዎች የጋንዲ ህይወት እጅግ ይመስጠኛል፡፡ ይህንን የምለው ለሐሰሳዬ እጅግ በሚቀርበው ምልከታው ነው፡፡ ከግለ ታሪኩ እንደምንረዳው ጋንዲ የደረሰበት ሳትያግራሃ (Satyagraha) ራስን በጥልቅ በመርመርና የሌሎችን ነጽሮተ ዓለሞች (ክርስትና ፣ እስልምና ፣ ዞራስተር፣ ሂንዲይዝም፣ ቴኦሶፊዝም፣ የሊዮ ቶልስቶይ የአለማቀፋዊ ወዳጅነት) ለራስ ፍለጋ ቀለብ በማጥናት ነው፡፡ አንዳንዶች የሌላውን እምነት ለማዋደቅ እንደሚያጠኑት አንጻራዊ ትምህርተ መለኮት(comparative theology) ወይም ግራ የገባው ቅየጣ(syncretism) ሳይሆን የግል እምነትን የጋራ ከሆነው ምህዳር ጋር እንዴት ያለተቃርኖ መምራት የሚደረግ ሙከራ ነው፡፡ ይህም ሀሳባዊነትና ቁሳዊነት መሀል ያለ ኃላፊነት የሚሰማው የአንድ ቅን ሰው ጉዞ ነው፡፡ ነውጥ አልባ ትግልን የሚያስመርጠው የሀይል ሚዛንን በመመልከት የሚደረግ ስሌት ወይንም የተጻጻሪውን አካል የነውጥ ባህሪ ምዘና አይደለም፡፡ በጦር ሜዳ የውጊያ ስልትህን የሚቀይሰው የጠላትህ አቅምና ባህሪ ነው ይባላል፡፡ ነውጥ አልባ ትግል ግን ከዚህ በተቃራኒ የሚወስድ ከውስጥ የሚመነጭ ምንም አይነት ጉልበትን ላለመጠቀም ለራስ የሚገባ ቃል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችም ለወራት በጥንቃቄ የተሞላና በፈጠራ የታገዘ (creative) የትግል ሂደት ውስጥ አልፈዋል፡፡ ይህ ዲሲፕሊን የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን በማሰርና ብዙ ጠብ አጫሪ ትንኮሳዎችን በመሸረብ ሊሰበር አልቻለም፡፡ አንዳንድ የተቃውሞ ሂደቶች እጅግ ከማስደመም አልፈው “Today, Am Muslim” ብለን እንድንል በፍቅር አስገድደውናል፡፡ ይህ ሂደት በሀገራችን ያለውን የዴሞክራሲ ሂደት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እንደሚያሳድገው እምነቴ የጸና ነው፡፡ ያለአመጽ የሚደረግ ማንኛውንም ነውጥ አልባ ትግል እደግፋለው፡፡ ሶስተኛው ተቃውሞውን የምደግፈበት ምክንያት በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ላይ ኢፍትሀዊነት እየተፈጸመ ነው ብዬ ስለማምን ነው፡፡ የእምነት ተቋማቸውን ማስተዳደር ተከልክለዋል ይህ ኢፍትሐዊነት ነው ስለዚህ እቃወመዋለው፡፡ አህባሽ የተባለ ባዕድ ትምህርት በተቋማቸው ላይ እየተጫነ ነው ይህም ጭቆና ነው ስለዚህ እቃወመዋለው፡፡ ዝምታው ይሰበር ዘንድ ለመነሻ ይህንን ጻፍኩኝ፡፡ ዝምታው ይሰበር ድምጻችንም ይሰማ! Injustice anywhere is a threat to justice everywhere!
Posted on: Fri, 30 Aug 2013 13:39:26 +0000

Trending Topics



Recently Viewed Topics




© 2015