ሕልሙን የቢሾፍቱ ሐይቅ ያጨናገፈው - TopicsExpress



          

ሕልሙን የቢሾፍቱ ሐይቅ ያጨናገፈው እግር ኳስ ተጨዋች እንደማንኛውም የቢሾፍቱ ከተማ ታዳጊዎች ኳስ ሲያንከባልል ማደጉ ይነገርለታል፡፡ በቢሾፍቱ ከተማ ቀበሌ 10 ተወልዶ ያደገው ወጣቱ እግር ኳስ ተጨዋች መስፍን ሁሴን (ሳዳም)፣ ለእግር ኳስ የነበረውን ጥማት ለማርካት ከልጅነቱ ጀምሮ በቶማስ ወልደ ሚካኤል አሠልጣኝነት መሠረታዊ የእግር ኳስ ክህሎትን በፕሮጀክት አጣጥሟል፡፡ የ19 ዓመቱ መስፍን የፕሮጀክት ሕይወቱን በተገቢው መንገድ ተከታትሎ፣ ከ2002 አስከ 2004 ድረስ ተወልደ ላደገበት ቀበሌ 10 እና 07 ተጫውቶ፣ ከዚያም ባለው የኳስ ክህሎት የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ መልምሎት በ2005 ለክለቡ ተስፋ ቡድን በመጫወት ላይ እንደነበር የክለብ ጓደኞቹ ይናገራሉ፡፡ በክረምቱ ምክንያት ለዕረፍት ቤተሰቦቹ ወደሚገኙበት ቢሾፍቱ ያመራው መስፍን፣ ነሐሴ 14 ቀን 2005 ዓ.ም. አስደንጋጩን የሕይወት ገጠመኝ ሊያስተናግድ ተገዷል፡፡ ከሰፈሩ ልጆች ጋር በመሆን በቢሾፍቱ ሐይቅ ዋና ለመዋኘት ወደ ስፍራው ያመራል፡፡ ሐይቁ ጋር ደርሰውም ከወትሮው በተለየ መልኩ በጎማ እየዋኘ ሳለ ጎማው በድንገት ያመልጠዋል፡፡ በድንጋጤ ሲወራጭ ወደ ውስጥ ሰምጦ ሕይወቱ ማለፉን ባልደረቦቹ አስረድተዋል፡፡ የተጨዋቹን አስከሬን ለማውጣት በርካታ ሙከራዎች ቢደረጉም፣ ነገሩ እንዲህ ቀላል ሊሆን እንዳልቻሉ የሚናገሩት የመስፍን ጓደኞች፣ ከአምስት ቀን በኋላ ነሐሴ 19 ቀን 2005 ዓ.ም. ከቀኑ ስድስት ሰዓት ላይ ሊገኝ እንደቻለ ነው ያስረዱት፡፡ የሟቹ ቤተሰቦች፣ አብሮ አደጎችና የሰፈር ሰዎች ከልጅ እስከ አዋቂ ለአምስት ቀን ያህል በሐይቁ ዳር ቀንና ማታ ሲጠባበቁ ቆይተው ከብዙ ድካምና ልፋት በኋላ በስድስተኛው ቀን የተገኘው አስከሬን ግብዓተ መሬቱ ነሐሴ 20 ቀን 2005 ዓ.ም. በቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን መፈፀሙም ታውቋል፡፡
Posted on: Wed, 28 Aug 2013 21:01:01 +0000

Trending Topics



Recently Viewed Topics




© 2015