የክሬዲት መለኪያዎቻችን ክፍል - TopicsExpress



          

የክሬዲት መለኪያዎቻችን ክፍል ሁለት ስለክሬዲት መለኪያዎቻችን (Credit Score) ተደጋግመው የሚነሱ ጥያቄዎች ውድ አንባቢዎቼ እንደምን ሠንብታችዋል፡፡ በክፍል አንድ ጽሁፌ በ (Jan.8 /2013) እንዴት ከምንም ተነስተን የክሬዲት ውጤታችንን እናጐለብታለን? በሚል ርእስ ጠቃሚ ነጥቦችን አግኝተናል፡፡ በክፍል ሁለት ጽሁፌ ደግሞ ስለክሬዲት መለኪያዎቻችን ተደጋግመው የሚነሱትን ጥያቄዎች እና እነሱን አስመልክቶ የተመለሱትን እንደሚከተለው አቅርቤላችዋለው፡፡ ጥያቄ- 1. ቤት፣ መኪና ወዘተ ለመግዛት ስንፈልግ ዝቅተኛ የሆነ የወለድ መጠን ለማግኘት ወደ ተለያዩ የአበዳሪ ቢሮዎች እንሄዳለን፡፡ ይህ በክሬዲት ውጤታችን ላይ የሚያመጣው ለውጥ አለ? መልስ - የብድር መጠይቁን በ14 ቀናት ውስጥ ካገኙ በክሬዲት ውጤትዎ ላይ ልዩነት ላያመጣ ይችላል፡፡ አንዳንድ አበዳሪዎች እንዲያውም እስከ 45 ቀናት የጊዜ ገደብ አላቸው፡፡ ስለዚህም አበዳሪ አካላቶችን ቀጥታ መጠየቅ ይኖርብዎታል፡፡ ለጠቅላላ ግንዛቤዎ እንዲሆንልዎ ቤት ወይም መኪና ለመግዛት ብድር ሲጠይቁ ፣ ክሬዲት ካርድ ለማውጣት ማመልከቻ ሲያገቡ በክሬዲት ውጤትዎ ላይ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጥበት (Hard Inquiry) በመባል ሲታወቅ ለአንድ ዓመት በክሬዲት ውጤትዎ ላይ ተጽእኖ ያሳድራል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ትኩረት የማይሰጥበት (Soft Inquiry) በመባል የሚታወቀው በክሬዲት ውጤትዎ ላይ ምንም ተጽእኖ የማያመጣ የመጠይቅ አይነት ሲሆን እንደምሳሌም የሚከተሉትን ማስቀመጥ ይቻላል፤ የክሬዲት ሪፖርትዎን ለማየት ሲፈልጉ፣ የንግድ መስሪያ ቤቶች ለፕሮሞሽን ሲጠቀሙበት የመሣሠሉትን ያጠቃልላል፡፡ ከላይ ያስቀመጥናቸው ሁለቱ መጠይቅ አይነቶች (Inquires) በክሬዲት ታሪካችን ላይ ለሁለት ዓመት ተያይዘው ይቀመጣሉ፡፡ ጥያቄ - 2. እዳዎችን በጊዜው ባልከፈልን ቁጥር (Late Payment) የክሬዲት ውጤታችን በምን ያህል ይጐዳል? መልስ - የከፈልነው እዳችን በተሰጠን የክፍያ ጊዜ ካልሆነ (Late Payment) እንደ FICO የውጤት አመዘጋገብ ሊያመጣ የሚችለው ተጽእኖ ካለን የክሬዲት ውጤታችን ጋር የተለያየ ይሆናል፡፡ ለምሣሌ ግለሰብ ቁጥር አንድ የክሬዲት ውጤቱ 680 የሆነና ለ30 ቀናት ሌላ አንድ (Late Payment) ያለው ከ60-80 የክሬዲት ውጤት ያጣል፡፡ ሌላ ግለሰብ የክሬዲት ውጤቱ 780 የሆነ ከዚህ ሌላ የ(Late Payment) የሌለው ከ90-110 የክሬዲት ውጤት ያጣል ይላል፡፡እዚህ ላይ ሊረዱት የሚገባው የክሬዲት ውጤቱ 780 የሆነው ግለሰብ ትልቅ ቅጣት የደረሰበት የአዋቂ አጥፊ ተብሎ ስለሚቆጠር ነው፡፡ ጥያቄ-3. ለአፖርትመንት የምንከፍለው ወራዊ ክፍያ ለክሬዲት ውጤት የሚያመጣው ውጤት አለ ወይ? የአፓርትመንት ውል ብናፈርስ ምን ሊሆን ይችላል? መልስ- እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት ለአፓርትመንት የምንከፍለው ወራዊ ክፍያ በመልካምነት ያለን የክፍያ ሂደት ለክሬዲት ቢሮ አይደርስም፡፡ አሁን ግን ካሉ የክሬዲት ቢሮዎች ውስጥ አንዱ የሆነው ኤክስፔሪያን (Experian Credit Bureau) የኪራይ ቢሮውን (Rent Bureau) ገዝቶታል፡፡ ይህ የኪራይ ቢሮ ከአፓርትመንት ባለቤቶች የሚሠበሰበውን የተከራዬች ታሪክ አሳልፎ ይሰጣል ማለት ነው፡፡ በዚህም መሠረት የክሬዲት ውጤታችን ላይ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል፡፡ የአፓርትመንት ውል ማፍረሰን በተመለከተ በውሉ መሠረት የምናቀርበው አሳማኝ የማፍረሻ ማስረጃ ካለን ለምሣሌ ከፓሊስ ደህነታችንን በሚያጓድል ዙሪያ አለበለዚያም ደግሞ ለምናፈርሰው ውል ቅጣታችንን በውሉ መሠረት የምንከፍል ከሆነ ውሉን ማፍረስ እንችላለን፡፡ ይህንን ካላደረግን ግን ሕጋዊ በሆነ መልኩ የምንጠየቅ መሆኑንና የክሬዲት ቢሮዎች አለመክፈላችንን ከ (Collection Bureau) ስለሚያገኙት የክሬዲት ውጤታችንን በአሉታዊ መልኩ ሊያስቀምጡት ይችላሉ፡፡ ጥያቄ - 4. የስልክ ክፍያዬ በክሬዲት ውጤቴ ላይ የሚያመጣው አስተዋጽኦ አለ? መልስ- በአግባቡ ለምንከፍለው የስልክ ክፍያችን ለምንፈልገው የክሬዲት ውጤታችን የሚያደርገው አስተዋጽኦ ምንም የለም፡፡ ምክንያቱም ለክሬዲት ውጤት አስተዋጽኦ ከሚያደርጉት ውስጥ ስላልተካተተ ነው፡፡ ነገር ግን ያልተከፈለ የስልክ እዳ ካለን የስልክ ካንፓኒው ወደ ሶስተኛ ወገን (Collection Agency) እዳችንን ስለሚልከው የክሬዲት ውጤታችንን ሊያበላሸው ይችላል፡፡ ጥያቄ- 5. የክሬዲት ውጤቱ የተበላሸበት እንዴት ማስተካከል ይቻላል? መልስ- የተበላሸ የክሬዲት ውጤት ለማስተካከል የራስ ጊዜንና ጥረትን የሚጠይቅ እንደመሆኑ የሚከተሉትን ነጥቦች ደረጃ በደረጃ ወደተግባር መለወጥ ይጠበቅብዎታል፡፡ ሀ. የክሬዲት ሪፖርትዎን ግልባጭ ከዋና ዋና የክሬዲት ቢሮዎች (Experian, Equifax and TransUnion) ማግኘት ወይንም በመረጃ መረብ https://annualcreditreport ውስጥ በመግባት የሶስቱንም ቢሮዎች በአንዴ ማግኘት ይቻላል፡፡ ለ. ያገኘነውን ሪፖርት እያንዳንዱን በጥሞና መመልከትና የጽሁፍ ስህተት ካለው ለክሬዲት ቢሮዎች በመደወል እንዲስተካከል ማድረግ ነገር ግን የኛ ጉድለት ያለበት ከሆነ እንደ ክብደቱ በዝርዝር ማስቀመጥ፡፡ ሐ. ክብደት ለሰጠነው ወይም በክሬዲት ውጤታችን ላይ ትልቅ ጉዳት ያደረሰብንን ቅድሚያ በመስጠት በተቻለ መጠን ሙሉ በሙሉ መክፈል፡፡ ከፍለን የጨረስነውን የክሬዲት ካርዶቻችንን ሳንመልስ (ሳንዘጋ) ማስቀመጥ፡፡ መ. ከዚህ በኋላ ለሚመጡ የክሬዲት እዳዎች ሙሉ በሙሉ አለበለዚያም ከዝቅተኛው መክፈል ካለብን በላይ መክፈልን ማዳበር፡፡ ሠ. አቅማችንን በደንብ ማወቅ ለወደፊት ለምንገዛቸው ማንኛውም ብድር እንደምንከፈለው እርግጠኛ መሆን፡፡ ከላይ በተፃፉት የዘወትር ጥያቄና መልሶቻቸው ላይ ጠቃሚ ቁምነገሮች ያገኙ ይመስለናል፡፡ እርስዎ ደግሞ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ለለት ከለት እንቅስቃሴዎ መሠረት ለሆነው አንዱ የክሬዲት ውጤትዎ አትኩሮት ይስጡ፡፡ ለዚህም አምላክ ይርዳን፡፡ Source - credit.about/od/creditscorefaq/Credit_Score_Frequently_Asked_Questions.htm livestrong/article/67211-fix-credit-score-legally/ ከድርሻዬ
Posted on: Sun, 07 Jul 2013 21:01:55 +0000

Trending Topics



Recently Viewed Topics




© 2015