የፓን አፍሪካኒዝም ራዕይ ጭንገፋ! (Geezbet) - TopicsExpress



          

የፓን አፍሪካኒዝም ራዕይ ጭንገፋ! (Geezbet) ክፍል አንድ ምዕራባዊያን አፍሪካን በበጎ ነገር አያነሷትም፡፡ የቀደምት ስልጣኔዋንም አምነው አይቀበሉትም፡፡ አፍሪካዊያኑም ቢሆኑ ስለማንነታቸውና ስለታሪካቸው ያላቸው እውቀት ፈረንጆች አፍሪካን ከሚያውቋት እጅግ ያነሰ ነው፡፡ ይህ ነገር ደግሞ አሁን አፍሪካ ካለባት ችግር በተጨማሪ ነገሩ የገለባ እሳት ሆኖባታል፡፡ አፍሪካ ባንድ ወቅት ኃያል ሃገር ነበረች፡፡ ነገር ግን ያ ስልጣኔዋ ተሸመደመደና ወደ ጨለማው ዘመን ገባች፡፡ የስልጣኔ መሽመድመድ በታሪክ አፍሪካ ብቻ ሳትሆን አውሮፓንም ደቁሷታል፡፡ ምስጋና ይግባቸውና የሰሜን አፍሪካ ሙሮች (Moors)፣ በሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደ አውሮፓ ተሻግረው፣ ጨለማ ውስጥ የምትገኘውን አህጉር አቀኑ፡፡ ከዚያ በኋላ አውሮፓ ሰለጠነችና አፍሪካን ተቀራመተች፡፡ ይህንን የአፍሪካ ቅርምጥ የአብርሆት (Enlightenment) ዘመን ልሂቃን የሚባሉት ጭምር ደግፈውታል፡፡ የአፍሪካ ህዝብ ሰብአዊ መብቱ ተገፎ ሰው ያለመሆኑ ታወጀ እና ለባርነት ተጋዘ፣ ተገረፈ፣ ተሰቃየ፣ ተሰቀለ፣ ታደነ፣ ታነቀ፣ ተገደለ፣ ንብረቱ ተዘረፈ፣ የአገር ባለቤትነቱን ተነጠቀ፣ ሳይፈልግ የወራሪዎቹን ባህል፣ ትምህርት፣ ኃይማኖት እንዲቀበል ተገደደ ………. ምን ያልሆነው አለ? እናም ይሄንን ግፍ አሽቀንጥረው ለመጣል ሃሳብ ያላቸው ጥቁር ልሂቃን በየቦታው ማኮብኮብ ጀመሩ፡፡ በመጀመሪያ ሰለ እነዚህን ንቅናቄዎች እና ኢትዮጵያኒዝም ትንሽ እንመለከታለን፡፡ ከዚያም ወደ ፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ እና ዓላማ፣ በመጨረሻም የፓን አፍሪካኒዝም ራዕይ እንዴት በአፍሪካዊያን አምባገነን መሪዎች እንደጨነገፈ በሶስት ተከታታይ ክፍሎች እንመለከታለን፡፡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ በደቡብ አፍሪካ በነጮች ይጨቆኑ የነበሩት እና በእምነቱ ውስጥ ምንም ቦታ ያልተሰጣቸው ጥቁሮች ከአንግሊካን እና ሜቶዲስት ደብር (Church) ተገንጥለው በውጣት ኢትዮጵያዊ ደብር (Ethiopian Church) መሰረቱ፡፡ በሰበካቸው ውስጥም “አፍሪካ ለአፍሪካዊያን” የሚል ነበረው፡፡ ይህም እንቅስቃሴ ኢትዮጵያኒዝም የሚባል አስተሳሰብ እንዲጀመር ረድቷል፡፡ የዌስልያን ሚኒስተር ማንጌና ሞኮን (Mangena Mokone) ኢትዮጵያኒዝም የሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ እንደተጠቀመ ብዙዎች ያምናሉ፡፡ የኢትዮጵያኒዝም እሳቤ ወደ ምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ናይጄሪያ፣ ጋና፣ ካሜሮን፣ ሮዶዥያና ሌሎችም አንሰራርቶ ነበር፡፡ ከአፍሪካ ውጭ ደግሞ ይህ እሳቤ በካረቢያን እና ሰሜን አሜሪካ እንደሰደድ እሳት ተስፋፍቶ ነበር፡፡ አንዳንድ ጸሐፍት ኢትዮጵያኒዝም የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ ለማብራራት እንደሚያስቸግር ቢያትቱም ዋና ጽንሰ ሃሳቡ ኃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ፍልስፍናን ያካተተ ነው፡፡ በሃይማኖታዊው ካየነው ጥቁሮች በነጮች የበላይነት የሚመራውን ደብር ትተን፣ የራሳችንን ከማንነታችን ጋር ትስስር ያላትን አፍሪካዊት (ኢትዮጵያዊት) ደብር እንመስርት የሚል ነው፡፡ ፖለቲካዊው ደግሞ በአለም የሚገኙ ጥቁሮች የነጮችን የፈላጭ ቆራጭ ገዥነትን ለመገርሰስ ኢትዮጵያን እንደ አርዓያ በመውሰድ የሚደረግ እንቅስቃሴ ነበር፡፡ በተለይ የአድዋ ድል፣ የኢትዮጵያ ቀደምትነት ስልጣኔ እና በመጽሐፍ ቅዱስ ስሟ መጠቀሱ ለኢትዮጵያኒዝም እሳቤ እና ለፓን አፍሪካኒዝም ፍልስፍና ጉልህ አስተዋጽኦ ነበራቸው፡ ፓን አፍሪካኒዝም፡- በመላው ዓለም የሚገኙትን አፍሪካዊያን አንድነት (ሶሊዳሪቲ) የሚቀሰቅስ ርዕዮተዓለም ነው፡፡ ፓን አፍሪካኒዝም መነሻውን ከጥንት የአፍሪካዊያን ስልጣኔ ጋር ያይዛል፡፡ ጥቁሮች ከጥንት ጀምረው እስካሁን ይዘውት የመጡትንና ጥንት የነበሩትን ታሪካዊ፣ ባሕላዊ፣ ኪነ-ጥበባዊ፣ መንፈሳዊ፣ ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ እሴቶችን በሕዝብ ዘንድ ማስረጽ አንደኛው ዓላማቸው ነው፡፡ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄዎች ቀደም ሲል የተጀመሩ ቢሆንም ዘመናዊው የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ የተጀመረው ግን በ1887 በትሪኒዳዱ የህግ ምሁር ሄነሪ ሲልቬስተር ዊሊያምስ “አፍሪካን አሶሴሽን” በሚል ስያሜ ነበር የተቋቋመው፡፡ እዚህ ላይ (ስለ መጀመሪያው የፓን አፍሪካን መስራች) በታሪክ ሰዎች ዘንድ ልዩነት አለ፡፡ አንዳንድ የታሪክ መጽሐፍት ላይ (ጸሐፊዎች) የመጀመሪያው የፓን አፍሪካን መስራች (ጽንሰ ሃሳብ አመንጭ) ላይቤሪያዊው መምህር፣ ጸሐፊ፣ ዲፕሎማትና ፖለቲከኛ ኤድዋርድ ዊልሞት ብላይደን ነው ሲሉ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ሄነሪ ሲልቬስተር ዊሊያምስ ነው ይላሉ፡፡ በአፍሪካም ይህን የፓን አፍሪካኒዝም አስተሳሰብ ካስፋፉትና ድርጅታዊ መሰረት ከሰጡት አንዱ የማላዊው ዜጋ የነበረው የባብቲስት ሚሲዮናዊ ዮሴፍ ቡዝ ነበር፡፡ የፓን አፍሪካን የመጀመሪያውን ጉባኤም በሐምሌ ወር በ1900 ለንደን ላይ በሄነሪ ሲልቬስተር ዊሊያምስ አስተባባሪነት ከአፍሪካ፣ ከዩናትድ ስቴትስ፣ ከካረቢያን እና ከአውሮፓ ሃገራት በተውጣጡ 32 ተወካዮች ተካሄደ፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ ከአፍሪካ የጋና (ጎልድ ኮሰት)፣ ሴራሊዮን፣ ላይቤሪያ እና ኢትዮጵያ ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡ የኢትዮጵያው ንጉሰ ነገሰት ዳግማዊ ምኒሊክ የሃይቲውን ቤኒቶ ሲልቪያን ወክለው ልከው ነበር፡፡ በዚሁ ስብሰባ ፓን አፍሪካን አሶሴሽን የሚል ድርጅትም አቋቋሙ፡፡ ከተሰብሳቢዎቹ አንዱ ታዋቂው አፍሮ አሜሪካዊው ምሁር ዱቦይስ (ዱ ቧ) ተገኝቷል፡፡ ዱቦይስ ከሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ በማህበራዊ ጥናት ዶክትሬቱን ያገኜ ሲሆን በአሜሪካም በጥቁሮች ታሪክ የመጀመሪያ ጥቁር ሰው ነው ደኮትሬት በማግኜት፡፡ በአትላንታ ዩኒቨርስቲም የታሪክ፣ ማህበራዊ ሳይንስ (ሶሲዎሎጅ) እና ምጣኔ ሃብት ፕሮፌሰር ነበር፡፡ ዱቦይስ የአሜሪካን ጥቁሮች በማንቃት በኩል ያደረገው ትግል እጅግ ከፍተኛ ነበር፡፡ ብዙ መጽሐፍትን ጽፏል፡፡ ታላቅ ስራው (Magnum Opus) ተደርጎ የሚወሰደው Black reconstruction in America ሲሆን ሌላው ተወዳጅ ስራው ደግሞ The Souls of Black Folk ነው፡፡ የ National Association for the Advancement of Colored People (NAACP) መስራች ሲሆን የዚሁ ድርጅት ልሳን ለሆነው The Crisis ዋና ኤዲተር ነበር፡፡ ፓን አፍሪካን ከመሰረቱት መካከል ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ በ1913 የኢትዮጵያ ኮኮብ (The star of Ethiopia) የሚል ተውኔት ደርሶ ለህዝብ እንዲታይ አድርጓል፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያን “የሰው ልጆች ሁሉ እናት (መፈጠሪያ)” ብሎ ይጠራት እና ያስተምር ነበር፡፡ የዓለም ስልጣኔ ሁሉ ከናይል ሸለቆ (ግብጽና ኢትዮጵያ) እንደተጀመረም ያቀነቅን ነበር፡፡ የፓን አፍሪካን እንቅስቃሴም ለግማሽ ምዕተ ዓመት ያህል መርቷል፡፡ ከለንደኑ ስብሰባ በኋላ አራት የፓን አፍሪካን ስብሰባዎች (በ1919 ፓሪስ፣ በ1921 ሎንዶንና ብራሰልስ፣ በ1923 ሎንዶንና ሊዝበን፣ በ1927 ኒው ዮርክ) የተዘጋጁት በዚህ ምሁር መሪነት ነበር፡፡ ያለ ዱቦይስ አሰተዋጽኦ ፓን አፍሪካኒዝም ወይም በተዘዋዋሪ የአሁኑ አፍሪካ ሕብረት ምን አልባትም ላይኖር ይችላል፡፡ የሚገርመው የኢትዮጵያና የአፍሪካዋያን ብዙ መገናኛ ብዙሓን ስለዚህ ጎምቱ የጥቁር ምሁርና የፓን አፍሪካን አባት ሚና ሲናገሩ፣ ሲጽፉ ወይም ሲዘክሩ አይታይም፡፡ ዱቦይስ እና ኩዋሜ ንኩርማህ በፓን አፍሪካን ምስረታ ጉዳይ የሚነጻጸሩ አይደሉም፡፡ ርቀታቸው የሰማይና የምድር ነው ብሎ የዚህ ጦማር ጸሀፊ ያምናል፡፡ ንኩርማህ፣ጁሊየስ ኒሬሬ፣ ጆሞ ኬንያታ ወዘተ. በ1945ቱ የማንቸስተሩ ፓን አፍሪካን ስብሰባ ላይ የተገኙ የርዕዮቱ ልጆቹ ናቸው፡፡ በርግጥ ከማንቸስተሩ የፓን አፍሪካን ስብሰባ በኋላ መሪነቱ በአፍሪካዊያን እጅ ገብቷል፡፡ ዱቦይስ በሶሻሊዝም ፍቅር ጋር እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ የወደቀ ነበር፡፡ የሶሻሊዝም ፍልስፍናው እንዳልገባው ቢናገሩም እሱ ግን ካፒታሊዝም የሰው ልጆች ዘረኛ እንዲሆኑ አድርጓል ይላል፡፡ እንም ዘረኝነትን ለማስቀረት ሶሻሊዝም ፍቱን መፍትሔ ነው ብሎ ያምናል፡፡ በዚህ ምክንያትም አሜሪካ አንቅራ ነበር የምትጠላው፡፡ በ1957 ጋና ነጻነቷን ስታገኝ የክብር እንግዳ አድርጋ ጠራችው፡፡ ነገር ግን አሜሪካ ጋና አትሄዳትም አለችና ፓስፖርቱን ቀማችው፡፡ ነገር ግን በ1960 ፓስፖርቱን ስላገኜ ወደ ጋና ሄደ፡፡ እናም ለጋና የሪፓብሊክ ምስረታ በዓል ላይ ተገኘ፡፡ በዚሁ ሰዓትም ከንኩርማህ ጋር ኢንሳክሎፒዲያ አፍሪካን ለማዘጋጀት ተስማሙ፡፡ በጀቱም በጋናዊያን መንግስት ነበር የሚሸፈነው፡፡ እናም በ1961 ከአሜሪካ ሚስቱን ይዞ በመምጣት ጋና ከተመ፡፡ የኢንሳክሎፒዲያውን ስራም ጀመረ፡፡ በ1963 አሜሪካ ፓስፖርቱን ለማደስ ፈቃደኛ ስላልሆነች የክብር እንግዳ ሆኖ ጋና ተቀመጠ፡፡ ነገር በዚያው ዓመት በነሃሴ ወር 1963 አክራ ውስጥ ሕይወቱ አለፈች፡፡ የተቀበረበት ቦታም የዱቦይስ መታሰቢያ ማዕከል ተብሎ ተሰይሟል፡፡ ሌላው ፓን አፍሪካን ሲነሳ ከመስራቾቹ ግንባር ቀደም የሆነውና አነጋጋሪው ማርቆስ ጋርቬይን እናገኛለን፡፡ አንዳንዶች ጋርቬይን የጥቁሮች ሙሴ እያሉ ይጠሩታል፡፡ ሙሴ እስራኤላዊያንን ከግብጽ ባርነት አላቆ ወደ ተስፋይቱ ምድር በመውሰድ ነጻ እንዳወጣቸው ሁሉ፣ ጋርቬይም ጥቁሮቹን ከጭቆናና ከባርነት አላቆ ወደ ተስፋይቱ ምድር አፍሪካ ለመውሰድ እና ጥቁሮችን አንድ ለማድረግ (ለማስተሳሰር) ያደረገው ተጋድሎ ግሩም ነበር፡፡ ፍልስፍናውም ጋርቬይዝም ይባል ነበር፡፡ ጋርቬይ ዓለም አቀፍ የጥቁሮች መሻሻል ማህበር፣ አፍሪካን ኮሚኒቲስ ሊግ፣ ብላክ ስታር ላይን ኮርፖሬሽን የሚባሉ ድርጅቶችን አቋቁሟል፡፡ ጋርቬይ የጥቁር አሜሪካዊያን ድርጅት በሆነው ኔሽን ኦቭ-ኢዝላም ያለው ክብር በጣም የገዘፈ እና እንደነብይም የሚመለከቱት ነው፡፡ በራስ ተፈሪያን እምነትም ከንጉስ ኃይለሥላሴ ቀጥሎ እንደ አምላክ (ነብይ) የሚቆጠር ሰው ነው፡፡ ነገር ግን እዚህ ላይ አንድ ማንሳት ያለብን ተቃራኒ ጉዳይ አለ፡፡ ጣሊያን ኢትዮጵያን ስትወር፣ ንጉስ ኃይለ ስላሴ ወደ እንግሊዝ የመሄዳቸውን ጉዳይ ጋርቬይ እንዲህ በቀላሉ አላለፈውም፡፡ ንጉስ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን በአደባባይ ለስጋቸው ሳስተው፣ ወገናቸውን ጦርነት ውስጥ ማግደው አውሮፓ እጃቸውን ሊሰጡ መጡ ብሎ ከመሳለቁም በላይ ቦቅቧቃና ፈሪ ብሎ ሰደባቸው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ በዝርዝር ሌላ ጊዜ ይዘን እንመጣለን፡፡ ጋርቬይ ነጮችን ስግብግቦች፣ ራስ ወዳዶች እና ፍቅር የለሾች ሲል በተለያየ ጊዜ ይገልጻቸው ነበር፡፡ ፍቅር፣ መተሳሰብና ለጋስነት ምንጩ አፍሪካ ግብጽና ኢትዮጵያ እንደሆነ ይሰብክ ነበር፡፡ በአሜሪካም በየጎዳነው እናንተ የሃያላን ልጆች ሆይ አትነሱም ወይ እያለ መሳጭ ንግግር ያደርግ ነበር፡፡ የሚገርመው ይህ ጥቁሮችን በመላው ዓለም ያንቀሳቀሰና ያነቃው ሰው (ጋርቬይ) ከዱቦይስ ጋር የከረረ ጠብ ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ ዱቦይስ በመጀመሪያ ብላክ ስታር ላይን የተሰኘውን የመርከብ ንግድ እቅድ (በማርከስ ጋርቬይ የተነደፈውን) ደግፎት ነበር፡፡ ጋርቬይ ጥቁሮች በሙሉ ወደ አፍሪካ ይመለሱ፣ በአፍሪካ አሜሪካዊያንም ይመሩ (ይስተዳደሩ) ሲል፣ ዱቦይስ ደግሞ ወደ አፍሪካ እንመለስ የምትለውን ሃሳብ እደግፈዋለሁ፡፡ ነገር ግን አፍሪካ በአፍሮ አሜሪካዊያን ይመሩ የምትለው ነገር ፈጽሞ የማይሆን ነው በማለት ይቃወመዋል፡፡ በዚህ ሁለት ጽንፍ ሃሳብ ባለመስማማት ባደባባይ እስከ መሰዳደብ ደርሰዋል፡፡ ዱቦይስ ጋርቬይን በአሜሪካና በመላው ዓለም ለሚኖሩ ጥቁሮች አደገኛ ጠላት ብሎ ከመፈረጁም በላይ ይሄ ሰው ከሃዲ ወይም እብድ መሆን አለበት ሲል ወርፎታል፡፡ ጋርቬይ ደግሞ ዱቦይስን “አንተ እኮ ነጭ እና የጥቁር ዲቃላ በተጨማሪም የነጭ ኔግሮ (White men’s nigger) ነህ’’ ይለው ነበር፡፡ ከዚህ ሌላ ጋርቬይ ብላክ ስታር ላይን የሚባለውን ድርጁቱን ለማጥፋት አሻጥር እየሰራብኝ ነው በማለት ይወቅሰው ነበር፡፡ ሌላው ለፓን አፍሪካኒዝም ድርጅት ምስረታ ትልቅ አስተዋጽኦ ካደረጉት መካከል ኢትዮጵያዊውን ቲ. ራስ መኮነን እናገኛለን፡፡ መኮነን የተወለደው ጉያና (Guyana) ውስጥ ሲሆን አያቱ ከሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ በአንድ ስኮትላዳዊ የማዕድን ሰራተኛ ነበር የተወሰደው፡፡ ስሙን የቀየረው (ቲ. ራስ መኮነን የተባለው) በሁለተኛው የጣሊያን ኢትዮጵያን ወረራ ጊዜ ነበር፡፡ ለምን ስሙን ቀየረ ካላችሁ፣ አፍሪካዊ ዝርያ እንዳለው ለማመልከት ነበር፡፡ አሜሪካ ኮርኔል ዩኒቨርስቲ ከተማረ በኋላ ያቀናው ወደ ዴንማርክ-አውሮፓ ነበር፡፡ ያኔ ታዲያ ኮፐንሃገን-ዴንማርክ ውስጥ የእርሻ ኮሌጅ ውስጥ እየተማረ እያለ ዴንማርክ ለጣሊያን የኢትዮጵያን ንጹሃን ሕዝቦች መግደያ የሚሆን ጅምላ ጨራሽ መርዝ አምርታ ትሰጣት ነበር፡፡ ይህንን ድርጊት ጋዜጦች ላይ ጦማር በመጻፍ በግልጽ ተቃወመ፡፡ 18 ወር ከተቀመጠባት ዴንማርክም ተባረረ፡፡ ከዚያ ወደ እንግሊዝ ተጓዘና በእነ ጆርጅ ፓድሞር በተመሰረተው ኢንተርናሽናል አፍሪካን ሰርቪስ ቢሮ ንቁ ተሳታፊ በመሆንና የቢሮውም የቢዝነስ ማናጄር በመሆን አገልግሏል፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ግን ወደ ማንቸስተር ዩኒቨርስቲ በማቅናት ታሪክ አጠና፡፡ በእንግሊዝም የስራ ፈጣሪ በሆን ብዙ ሆቴሎችን ከፈተ፡፡ ከጆርጅ ፓድሞር እና ኩዋሜ ንኩርማህ ጋር በመሆንም የ1945ቱን የፓን አፍሪካን ኮንግረስ ለማደራጄት ብዙ ደክሟል፡፡ በ1947 ፓን አፍሪካ የተባለ ህትመት ልሳን መሰረተና የአፍሪካን የቀን ተቀን ስቃያቸውንና ፍላጎታቸውን ለመላው አፍሪካዊያንና አሜሪካዊያን ያሰራጭ ነበር፡፡ በ1957 ጋና ነጻነቷን ስታገኝ መኮነን ከንኩርማህና ፓድሞር ጋር ሆኖ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ለመመስረት ወደ ጋና ሄደ፡፡ በ1966 ንኩርማህ መፈንቅለ መንግስት ከተካሄድባቸው በኋላ መኮነን ወደ እስር ቤት ተወረወረ፡፡ ከእስር የተፈቱት በጆሞ ኬንያታ ጥረት ነበር፡፡ ከዚያም ጆሞ ኬንያታ አገሬ አገርህ ነው በማለት ይመስላል ወደ ኬንያ ወሰዱት፡፡ ከዚያም የኬንያ ዜግነት ሰጥተው የአገሪቱ የቱሪዝም ሚነስተር አድርገው ሾሙት፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያዊ ዝርያ ያለውን ፓን አፍሪካኒስት ብዙዎቻችን አናውቅም፡፡ ምን አልባት የናይሮቢ ዩኒቨርሰትቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ኬኔት ኪንግ ከዘጠኝ ወር በላይ ሞኮነንን ቃለ መጠይቅ አድርጎ በ1973 ያሳተመውን Pan-Africanism from Within ማግኜት ብንችል የበለጠ ሰለማንነቱ ማወቅ ይቻል ይሆናል፡፡ ክፍል ሁለትን በሚቀጥለው ሕትመት ይዘን እንመጣለን፡፡ ቸር ሰንብቱ፡፡ geezbet
Posted on: Sun, 16 Jun 2013 10:36:10 +0000

Trending Topics



0px;"> THE TRIAL OF JESUS CHRIST IN THE DAY OF JUDGEMENT (For Muslims
To My Daughter, I look at your pictures and do not see the
WHATʻS THE CONCLUSION TO TWO KEY MISCONCEPTIONS REGARDING HAWAI`I
Trnyata Kekuatan militer Indonesia NO.15 Didunia, NO. 7 diasia

Recently Viewed Topics




© 2015