***ክብሬ የት ነው?*** (ሚራ) የሰው ልጅ - TopicsExpress



          

***ክብሬ የት ነው?*** (ሚራ) የሰው ልጅ የምድር ሁሉ ጌጥ ነው፡፡ ምድርና ውስጧ በሙሉ ለሰው ልጅ ተፈጥረዋልና በሁሉ ላይ ያዛል፣ በሁሉ ላይ ይፈርዳል፡፡ ምድርም ያለ ሰው ልጅ ምንምና ከንቱ ናት!!! የሰው ልጅ ትልቅና ክቡር ነው፤ ትልቅነቱንና ክብሩን ያገኘው ደግሞ ከራሱ ሳይሆን ከፈጣሪው ነው፤ ትልቅነቱንና ክብሩን ግን ማስጠበቅ የሚችለው ማንም ሳይሆን ራሱ ሰው ብቻ ነው፤ በራሱ ላይ ባለሙሉ ስልጣን ሹመኛ ነውና!!! የሰው ልጅ ሁሉን ይለምድ፣ ሁሉን ይማር፣ ሁሉንም ይመረምር ዘንድ ፈቃድም አቅምም አለው፡፡ ከለመደው፣ ከተማረው እንዲሁም ከመረመረው ነገር ውስጥ መልካሙን የመምረጥ፣ ክፉውን የመጣል (የማሻሻልም ሊሆን ይችላል) ተፈጥሮአዊ ችሎታም ተሰጥቶታል፡፡ ከባድ እንኳ ቢሆን በጊዜ ሂደት ሁሉም ይለመድና ከባዱ ቀላል ይሆናል፡፡ (ሕይወት ልምምድ ናት እንዲል ወዳጅ Biniyam) አንዳንድ ሰዎች “በእገሌ ክብሬ ተነካ፣ በእገሌ ክብሬ ተንቋሸሸ” ብለው ሆድ ሲብሳቸው ሲብስ ደግሞ እልህ ውስጥ ሲገቡ እናያለን፡፡ (የትም አትሂዱ እዚሁ ነኝ)፡፡ አነሰም በዛም ሁላችንም የዚህ አመለካከት ሰለባ ሆነን እናውቃለንና (ለዛውም በተደጋጋሚ)፡፡ ግን የምር የእኛ ሰዋዊ ክብር የት ነው ያለው? በማንስ ስልጣን ነው የሚመራው? በቃ ዝም ብሎ ማንም ይቀልድበት ዘንድ የተፈጠረ፣ ማንም በተናገረው ነገር የሚሰበርና የሚቆሽሽ ነው እንዴ? ሰው ሲያከብረን ብቻ ከፍ ከፍ የሚል፣ ሰው ሲያጣጥለን ደግሞ አፈር የሚበላ ክብር ነው እንዴ የተሰጠን? አዋቂ ስላልኩት ብቻ አዋቂ የሚሆን ማነው? ደደብ ስላልኩትስ የሚደድበው የትኛው ስብዕና ነው? እንደዛማ ከሆነ ክብራችን በእኛ ሳይሆን በሌሎች ቁጥጥር ስር ያለ፣ ሲፈልጉ የሚቀሙን፣ ሲያሻቸው የሚሰጡን ልግስናቸው ሆነ ማለት አይደለምን? እኔ ግን እላለሁ፡- ክብሬ በእኔ ዘንድ ናት፡፡ ከሰጠኝ ከፈጣሪ በቀር ማንም የሚቸረኝ ማንምም የሚነፍገኝ ተራ ንብረቴ እንዳልሆነም አውቃለሁ፡፡ ሌላውን ባለመናቅ ራሴን እስካከበርኩ ድረስ ማንም ክብሬን ሊገፈኝ አይችልም፡፡ እጅግ የበዛ ሙከራ እንኳን ቢኖር እኔ ራሴን አክብሬ ከቦታዬ እስካልተንቀሳቀስኩ ድረስ ሙከራው የሞካሪውን ክብር የሚገፍ ካልሆነ በቀር ከኔ አንዳች የክብር ቅጠል ሊቀነጥስ አቅም የለውም፡፡ ምክንያቱም ክብሬ በስልጣኔ ያለች ትልቅ ንብረቴ ናትና፡፡ ሰው ያሳየኸውን እሱኑ ላንተ መልሶ ያሳይሃል፡፡ ራሳቸውን ሳያከብሩ ከሰው ክብር የሚጠብቁ ሰዎች እጅግ ምስኪኖች ናቸውና ያሳዝኑኛል፡፡ ራሳቸውን ለመመልከት የሰው መስታዎት የሚያሳድዱ ሰዎች የዋሆች ናቸውና አንጀቴን ይበሉኛል፡፡ እኔም የዋህ ሆኜ ብዙ ጊዜ ራሴን በሰው መስታዎት ተመልክቸዋለሁ፡፡ ያገኘሁት እውነት ግን አንድ ነበር፡፡ እሱም እኔ አንዱ ሚራ እጅግ የብዙ መልክ ባለቤት መሆኔ ነበር፡፡ አልጨረስንም ብላለች Meri!!! ዛሬ እኔም አልጨረስኩም፡፡
Posted on: Fri, 28 Nov 2014 06:53:29 +0000

Trending Topics



Recently Viewed Topics




© 2015